ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።

18

ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎በምሥራቅ ጎጃም ዞን አነደድ ወረዳ በ2017 በጀት ዓመት ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው 43 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።

‎በወረዳው በበጀት ዓመቱ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከኾኑት መካከል የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። የመሠረተ ልማቶቹ የወረዳውን ሕዝብ ተጠቃሚነት በእጅጉ የሚያሳድጉ መኾናቸውን የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ አየለ ድረስ ተናግረዋል።

የመሠረተ ልማቶች በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው ኅብረተሰቡ እንደራሱ ሃብት እና ንብረት በመቁጠር መንከባከብ እና መጠበቅ እንደሚገባውም አቶ አየለ አሳስበዋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኅላፊ ገዳሙ መኮነን በከተሞች የሚሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ሢሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በአነደድ ወረዳ ለምርቃት የበቁ የልማት ሥራዎችም በዘላቂነት የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ገነት በቀለ መንግሥት ዘላቂ ሰላም ከማስፈን ጎን ለጎን ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እና የመሠረተ ልማቶችን እየገነባ መኾኑን ተናግረዋል። የተሠሩ የመሠረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸው የሕዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ለመመለስ የተሄደበትን የመንግሥትን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳየ እንደኾነም ገልጸዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የወረዳው ነዋሪዎችም መንግሥት የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ያደረገውን ጥረትም አድንቀዋል።
የተሠሩ የልማት ሥራዎችም የሚጠበቅባቸውን ግልጋሎት እንዲሰጡ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሮጀክቶች ለምረቃ እንዲበቁ የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ ለነበሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ለትውልድ የተመቼች ሀገር የማስረከብ አደራ ነው” የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ
Next article“ለመትከል ያቀድነው ዕቅድ ከታሰበው በላይ ተሳክቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)