“የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ለትውልድ የተመቼች ሀገር የማስረከብ አደራ ነው” የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ

14

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ24/2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ መሪዎች እና ሕዝቦቿ በመላው የሀገሪቱ ክፍል በመሰማራት የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ እየተሳተፉ ነው። መሪዎች በያሉበት ሁሉ አረንጓዴ አሻራቸውን እያሳረፉ፣ የተለያዩ የማትጊያ መልእክቶችንም እያስተላለፉ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ከመሥሪያ ቤታቸው መሪዎች እና ሠራተኞች ጋር በመኾን አረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉት የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ መርሐ ግብሩ ለትውልድ የተመቸች ሀገርን የማስረከብ አደራ ነው ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ ስለመኾኑም ተናግረዋል። አረንጓዴ ልማቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮን ምቹ በማድረግ የድካማችንን እየከፈለን ይገኛል ነው ያሉት።

“በመትከል ማንሰራራት” በሚል ንቅናቄ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሀገራችን ከድህነት ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ነውም ብለዋል ሚኒስትሩ። ማንሰራራት በአረንጓዴ ልማትም፣ በኢኮኖሚም፣ በማኅበራዊ እና በሁሉም ዘርፎች የሚገለጽ ነው ብለዋል።

የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ በአንድ ቀን ውስጥ በርካታ ችግኞችን በመትከል እንደ ሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚያኮራ ተግባር የሚፈጸምበት ስለመኾኑም ገልጸዋል።

የዛሬው ቀን የኢትዮጵያውያን ከመሪያቸው ጋር የመደማመጥ ልምድ፣ ጥሪን ተቀብሎ ሥራን የመፈጸም ባሕል እና ሥራን በውጤታማነት የመፈጸም ብቃት በተግባር የሚረጋገጥበት ነውም ብለዋል።

ለትውልድ የሚተርፍ አረንጓዴ አሻራችንን ለማስቀመጥ እድሉን በማግኘታችን እንኳን ደስ ያለን ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleእስከ ቀን 9:00 ሰዓት 648 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
Next articleከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።