አዲሱ የሞባይል ሰብስቴሽን ሥራ መጀመርም በኃይል እጥረት ምክንያት የቀዘቀዘውን የደብረ ታቦር ከተማ ምጣኔ ሀብት እንደሚነቃቃው ተመላከተ፡፡

238

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት የከተማዋን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡

ከደቡብ ጎንደር ዞን ሕዝብ የዘመናት ዋና ዋና የልማት ጥያቄዎች መከካል አንዱ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማግኘት ነበር፡፡ ጥያቄውን የሚመልስ 50 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስተላልፍ “ሞባይል ሰብስቴሽን” ደብረ ታቦር ከተማ ላይ ዛሬ ሥራ ጀምሯል። ይህም ከተማዋ ከ40 ዓመታት በላይ ከወረታ፣ ከአዲስ ዘመን እና ሌሎች ከተሞች ጋር ስትጋራ የነበረውን 14 ነጥብ 4 ሜጋ ዋት ብቻ ኃይል ለማሳደግና እጥረቱን ለመቅረፍ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችም ዛሬ የሞባይል ሰብስቴሽን ሥራውን አስጀምረዋል። የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ የደብረ ታቦር ከተማን የመልማት ጥያቄዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ አሳሳቢ የነበረውን የመብራት ችግር በተመለከተ ሲናገሩም “ከዘመናት በፊት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ መሠረት የተጣለባት ከተማ ለዓመታት ሻማ ይዛ እራት ስታበላ ማየት ጉዟችን ጤናማ እንዳልነበረ ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።

ደብረ ታቦር ታሪክ፣ ጥበብና ትምህርት የተገመደባት ለኢትዮጵያውያን የአንድነት ጥንስስ ከተማ መሆኗን ያወሱት አቶ ተመስገን የአጼ ቴዎድሮስ ራዕይ ለተገለጠባት ከተማ ያለመልማት ቁጭቱ ወደ ተሻለ ሥራ ሊመራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ደብረ ታቦርን ወደ ኢንዱስትሪና ታሪካዊ ቦታዋ ለመመለስ ይህ ትውልድ በኃላፊነት ስሜት መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ ሰብሳቢ አብርሃም በላይ (ዶክተር ኢንጂነር) የደብረ ታቦርንና የሌሎች አካባቢዎችን የኃይል ፍላጎት ፈጥኖ ለማሟላት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ከደብረ ታቦር ሕዝብ የመልማት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱን መመለስ ተችሏል ያሉት ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም አሁንም ሌሎች የከተማዋ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የፌዴራል መንግሥት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምህረቴ በበኩላቸው ደብረ ታቦር የአሌክትሪክ ኃይልን ለመኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ለኢንቨስትመት አማራጮች ማስፋፊያነት ለመጠቀም እየፈለገች የኃይል እጥረት ለዕድገቷ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ዘመናትን በተሻገረው የኃይል እጥረት ምክንያት ኢንዱስትሪዎች ሥራ ማቆማቸውን፣ ጥቂቶችም በወረፋ ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልጸዋል። አዲሱ የሞባይል ሰብስቴሽን ሥራ መጀመርም በኃይል እጥረት ምክንያት የቀዘቀዘውን ምጣኔ ሀብት እንደሚነቃቃው ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበኢትዮጵያ ተጨማሪ 129 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፡፡
Next articleበኩር ሰኔ 1/2012