
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ኢትዮጵያውያን በንቅናቄ ወጥተው ለትውልድ የሚተርፍ አረንጓዴ አሻራቸውን እያሳረፉ ነው።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መሪዎች እና ሠራተኞችም በጋራ በመኾን በአዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራቸውን እያሳረፉ ነው።
በዚሁ አካባቢ በችግኝ ተከላው ከተሳተፉ ሚኒስትሮች ውስጥ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ይገኙበታል።
የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ኢትዮጵያ የያዘችውን የአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብር ለማሳካት እና አካባቢን ለመጠበቅ ሁነኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
“አረንጓዴ አሻራ የሀገሪቱን የደን ሽፉን ከማሳደግ በተጨማሪ የኢትዮጵያውያንን ለሀገራዊ የልማት ፕሮግራሞች በጋራ የመቆም እና የመፈጸም ባሕል ያጎለበተ” ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ውጤት በሃብት ሲለካም ትልቅ ሃብት የተፈጠረበት ስለመኾኑ ጠቁመዋል። በመኾኑም መርሐ ግብሩ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ማኅበረሰቦች ለጋራ ዓላማ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከሀገር ግንባታ አንጻርም የጎላ ትርጉም አለው።
የገንዘብ ሚኒስቴር መሪዎች እና ሠራተኞችም በተከታታይ ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሲሳተፉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን