
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ነው።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ጉለሌ አካባቢ የአረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ዛሬ የተለየ ቀን ነው ብለዋል። ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ለአምራች ኢንዱስትሪው አስፈላጊ ነው ያሉት ሚኒስትሩ አካባቢው ሲያገግም እና ምርታመነቱ ሲጨምር ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት ኾኖ ያገለግላል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ የኢንዱስትሪ ዘርፉን እና የሌሎችን ውጤታማነት እንደሚያሳድግም ገልጸዋል። ለቱሪዝም መስህብነት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እንደሚያገለግልም አንስተዋል።
የችግኝ ተከላ ጥቅሙ አንድ እና ሁለት ብቻ አለመኾኑንም ገልጸዋል። በአንድ ጀንበር ለትውልድ የሚትርፍ ሥራ ነው የምንሠራውም ብለዋል።
ለትውልድ በሚተርፍ ዘመቻ ላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ባሕል እንዲኾን ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የመንግሥት ሥራ አይደለም የትውልድ፣ የዜጋ እና የሀገር ሥራ ነው ብለዋል። ዛሬ የሚተከለው ችግኝ ለመጭው ትውልድም የሚያገለግል መኾኑን ነው የተናገሩት።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን