
ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር እየተካሄደ ነው።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ መለሰ ሙላት በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ለምግብነት፣ ለውበት እና ለደን ልማት የሚጠቅሙ እንደኾኑ ነው የተናገሩት።
ከዚህ በፊት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢውን ብዝኅ ሕይወት ከመለወጥ ባሻገር ለተለያየ ጥቅም መዋል ጀምረዋል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመሥገን “በመትከል ማንሠራራት” በሚል መሪ መልዕክት የሚተከሉ ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ መንከባከብ ቀዳሚ ተግባር መኾኑን አስገንዝበዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተሳተፉ አካላትም ከዚህ በፊት የተከሏቸውን ችግኞች የት እንደደረሱ አስታውሰው በዚህ ዓመት የተከሏቸውንም እንደሚንከባከቡ ተናግረዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያም ከተከላ በኋላ የችግኞችን መጽደቅ ክትትል እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን