
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም “ለአረንጓዴ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልእክት መላው የኩባንያው ጽሕፈት ቤቶችን በማቀናጀት 500 ሺህ ችግኞችን የመትከል ሥራውን አስጀምሯል።
በኮርፖሬት፣ በዞን እና ሪጅን ደረጃ ከ4 ሺህ 900 በላይ የኩባንያው ሠራተኞችን በማሳተፍ በአዲስ አበባ በተመረጡ የተከላ ቦታዎች የችግኝ ተከላ ዘመቻ አካሂዷል፡፡
በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ እንጦጦ እና ሀምሊን ፊስቱላ ቅጥር ግቢ በተዘጋጁ ቦታዎች የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውኗል። የኩባንያው 18 ሪጅኖች ደግሞ በተረከቧቸው ቦታዎች ላይ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አካሂደዋል፡፡
ባለፉት ተከታታይ ስድስት ዓመታት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 805 አካባቢዎች ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራውን ማኖር ችሏል፡፡
በዚህም በአማካይ ከ82 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ችግኞችን በማጽደቅ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ በማልበስ በረሃማነትን እና ድርቅን በልምላሜ ለመቀየር የበኩሉን ጥረት አድርጓል። ከ23 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎችም ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡
ኩባንያው የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ እና የኢኮ ቱሪዝም ፕሮግራሞች ከ1 ነጥብ 03 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ አድርጓል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን