
ደብረ ብርሃን፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከማለዳው ጀምሮ አርሶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የንግዱ ማኅበረሰብና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መንገድ መርሐ ግብሩ እየተካሄደ ነው።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኅላፊ ታደሰ ማሙሻ ችግኝ ተከላው በጥሩ ተነሻኝነት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዞኑ የደን መመናመን በጥቅሉ የሥነ ምህዳር ከባቢ ላይ የሚፈጥረውን አደጋ በመረዳት ከተከላ እስከ ጥበቃ ጠንካራ ሰንሰለት በመፍጠር ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ለማስቀጠል እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ሥራችን የሠዉ ልጅ ተፈጥሮን በማክበርና በመንከባከብ ሕይወቱን ባማረ መንገድ መምራት እንዲችል የሚያግዝ ታሪካዊ ሥራ ነዉ ብለዋል፡፡
አካባቢያቸውን ከመራቆት በመታደግ ይልቁንም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ የቻሉ በርካታ አካባቢዎች በዞኑ መኖራቸውን ኅላፊው ገልጸዋል፡፡
በዞን ደረጃ የተሻለ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ባለበት አሳግርት ወረዳ የክልል እና የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት የችግኝ ተከላው እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ በጥረት አካባቢን በመቀየር በኩል ማሳያ ከተጠቀሰ የአሳግርት ወረዳ አንዱ ተሞክሮ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የአርንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ምቹ አካባቢን በመፍጠር ለመጪው ትውልድ የተሻለ ነገር የማስረከብ ግዙፍ ኅላፊነት መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን