
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
በማለዳው በጅማ ከተማ የአረንጓዴ አሻራቸውን ያሰረፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እኩለ ቀን ላይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ተራራ ላይ ችግኝ ተክለዋል።
በሥፍራው ኾነው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በየካ ተራራ አፈር እንዳይሸረሸር እርከን መሠራቱን ገልጸዋል። የሚተከሉ ችግኞች ወደፊት ዋጋ የሚያወጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
እስከ እኩለ ቀን ድረስ ከ500 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም ገልጸዋል። እንደ ጠዋቱ ሁሉ ተረባርበን ከሠራን ካቀድነው በላይ ልናሳካ እንደምንችል ጥርጥር የለውም ነው ያሉት።
በጀመርነው ፍጥነት እና ቁርጠኝነት ከቀጠልን በሚቀጥሉት ሰዓታት ዕቅዳችን እናሳካለን ብለዋል። እንቀጥል፣ እንተከል፣ እናቅድ ደግሞም እናሳካ ነው ያሉት።
ከፍጻሜ ውስጥ ነው ውጤት ያለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጭ ብለን ስላቀድን ሳይኾን ስንሠራው ነው ውጤት የሚመጣው ነው ያሉት።
እስካሁን የተከለ ድጋሜ እንዲተክል፣ ያልተከለም ወጥቶ እንዲተክል ጥሪ አቅርበዋል። በመትከል ፍሬ እያፈራን ነው፣ ውጤት እያመጣን ነው፣ እንድንተክል፣ እንድንበረታታ ዕቅዳችን እንድናሳካ አደራ እላለሁ ብለዋል።
እስካሁን ያለው ተስፋ ሰጪ መኾኑን እና እንደሚቀጥል ያለችውን እምነት ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን