
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 5 ሺህ 500 የላቦራቶሪ ምርመራ በ129 ሰዎች የኮሮናቫይረስ መገኘቱን ጤና ሚኒስቴር ገልጧል፡፡
በአጠቃላይ በሀገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 934 ደርሷል፡፡
ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከኮሮናቫይረስ ጋር በተገናኘ የአንድ የ80 ዓመት ኢትዮጵያዊት የአዲስ አበባ ነዋሪ ህይወት አልፏል። ሟቿ ወደ ሆስፒታል ለሌላ ህክምና በመጡ በአንድ ሰዓት ወስጥ ህይወታቸው ማለፉን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡ በአስክሬን ምርመራም የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል። በዚህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 20 ደርሷል፡፡
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ከአንድ እስከ 90 ዓመት የሆናቸው 75 ወንዶችና 54 ሴቶች ናቸው፡፡ ከአነዚህ ውስጥ 124 ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የአሜሪካ፣ የኤርትራ እና የሱዳን ዜጎች ናቸው፡፡
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 101 ከአዲስ አበባ፣ 10 ከአማራ፣ ስድስት ከሶማሌ፣ አምስት ከትግራይ፣ አምስት ከኦሮሚያ፣ አንድ ከሃረሪ እና አንድ ከጋምቤላ ክልሎች ነው፡፡
በሌላ በኩል ትናንት 19 ሰዎች (2 ከትግራይ ክልል፣ 6 ከአፋር ክልል፣ 1 ከሶማሌ ክልል እና 10 ከአዲስ አበባ) ከበሽታው አገግመዋል፤ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 281 ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መግባቱ ከተረጋገጠበት ዕለት እስከ ዛሬ 136 ሺህ 868 የናሙና ምርመራ ተደርጎ በ1ሺህ 934 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር መረጃ መላክታል፡፡