
ጎንደር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በላይ አርማጭሆ ወረዳ ችራ ቀበሌ እየተካሄደ ነው።
በችግኝ ተከላው ላይ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የላይ አርማጭሆ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሴ ማለደ በዞኑ በሚገኙ 15 ወረዳዎች የችግኝ መትከል መርሐ ግብሩ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሪ የሚተከሉ ችግኞችን ማኅበረሰቡ ባለቤት ኾኖ በመጠበቁ ባለፈው ዓመት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 86 ነጥብ 2 ከመቶ መጽደቅ መቻሉን ተናግረዋል።
አሁንም ይህንን ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል የሚተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ዋና አሥተዳዳሪው በችግኝ መትከል መርሐ ግብሩ የተሳተፉ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደምም ችግኞችን መተከላቸውን እና የተከሏቸውንም ችግኞች ሲንከባከቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የአርማጭሆ ወረዳ ነዋሪዎች እንደ ሀገር በዛሬው የችግኝ መትከል መርሐ ግብር በመሳተፋቸው ደስተኛ እንደኾኑ ነው ያስረዱት።
ነገ የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻለው ዛሬን በመትከል በመኾኑ በቀጣይም የአረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ተግባሩን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን