“አረንጓዴ አሻራ መላ ኢትዮጽያውያን ፈጥነው የገዙት ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ ነው” የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ርእሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ.ር)

11

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ ልማት በዓለም ፊት ቀዳሚ የሚያደርገው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ በመላ ኢትዮጵያ እና በሕዝብ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው። የሀገሪቱ መሪዎች ሕዝብን እያስተባበሩ ለትውልድ የሚተርፍ አሻራቸውን በየአካባቢው እያሳረፉ ነው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ.ር) በዞኑ ሀላባ ዞን ተገኝተው አሻራቸውን አሳርፈዋል። የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የሕዝብን አጠቃላይ ሕይዎት የሚለውጥ የልማት ሥራ ነው ብለዋል።

በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተያዘውን የመንግሥት ፕሮግራም ለማሳካትም ሁነኛ መንገድ ነው ብለዋል። ፕሮግራሙ እንዲሳካ አትክልት እና ፍራፍሬ ከጓሮ መቁረጥ፣ ውኃ እንደልብ ማግኘት እና ማልማት ያስፈልጋል፤ አረንጓዴ አሻራ ደግሞ ለዚህ ያበቃል ነው ያሉት።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ተከትሎ የተጠናከሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። በዚህም የነበረው የአየር ንብረት ቀውስ መሻሻል እየታየበት ነው፤ ዝናብ አጠር የነበሩ ቦታዎች በቂ ዝናብ እያገኙ ነው፤ የደረቁ ወንዞች ውኃ እንዲፈስስባቸው አስችሏል፣ የተራቆቱ አካባቢዎች ደን መኾን ጀምረዋል፤ ጎርፍ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ውኃን መያዝ ጀምረዋል ነው ያሉት።

በአረንጓዴ አሻራ ለምግብነት የሚውሉ ዛፎች ሲተከሉ ቆይተዋል፤ ይህም ከምግብ ፍጆታነት ባለፈ ወደ ገበያም በማውጣት ለኢኮኖሚ ምንጭነት እያገለገለ ነው ብለዋል። አረንጓዴ አሻራ መላ ኢትዮጽያውያን ፈጥነው የገዙት ትልቅ አጀንዳ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተፈጥሮን መጠበቅ የትውልድ አደራ ነው።
Next articleየሚተከሉ ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎችን ወደአረንጓዴነት እየመለሱ ነው።