
ሁመራ፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወፍ አርግፍ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን ጨምሮ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ተፈጥሮን በአረንጓዴ አሻራ በመጠበቅ የእርሻ ተግባራትን እያከናወኑ መኾኑን ችግኝ ሲተክሉ አሚኮ ያገኛቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች ላይ በንቃት ይሳተፉ እንደነበርም ነው የጠቆሙት።
ችግኝ በመትከላቸው አካባቢውን ከጎርፍ በመከላከል ለግብርና ሥራ ምቹ ኹኔታ እንደፈጠረላቸውም አስረድተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሀገርን ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር በችግኝ ተከላ በመሳተፋቸው ድርብ ኀላፊነትን እየተወጡ መኾኑን ማሳያ እንደኾነ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ97ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ኮረኔል ባቲ ቱኬ ገልጸዋል።
ተፈጥሮን መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ሥራ መኾኑን ጠቅሰዋል። “በሀገር አቀፍ ደረጃ 700 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀንበር ለመትከል በሚደረገው ርብርብ ላይ መሳተፍ የዜግነት ግዴታችን ነው” ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ ተፈጥሮን መጠበቅ የትውልድ አደራ መኾኑን ተናግረዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ተግባር በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ችግኝ እየተተከለባቸው ያሉ ተፋሰሶች ከዚህ በፊት የተራቆቱ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ከዓመት ዓመት በሚደረገው የችግኝ ተከላ እያገገሙ መኾኑን አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን