የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥተ ረቂቅ በጀት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

515

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 84ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በ2013 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ነው፡፡ በ2013 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ለፌዴራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች ብር 133‚321‚561‚063፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 160‚329,788‚483፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 176‚361‚602‚899፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 6,000,000,000 በጠቅላላ ብር 476‚012,952,445 (አራት መቶ ሰባ ስድስት ቢሊዮን አሥራ ሁለት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሁለት ሺህ አራት መቶ አርባ አምስት ብር) እንዲሆን የቀረበው ረቂቅ በጀት ምክር ቤቱ ከተወያየበት በኋላ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠልም የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ ደንብ በተመለከተ ነው የተወያየው፡፡ ወረርሽኙ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የግል ድርጅቶች ከሐምሌ 2007 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2012 ድረስ ባልተከፈለ የጡረታ መዋጮ ላይ ሊከፈል የሚገባውን መቀጮና ወለድ ሙሉ በሙሉ እንዲነሣ፤ የሚፈለግባቸውን ዕዳ ከከፈሉ በዕዳ ምክንያት የተያዙ ንብረቶችን ለድርጅቶቹ ለመመለስ የሚያስችሉ ተጨማሪ ርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

3. የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጡ የአስቸኳይ ጊዜ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ የተመለከቱ የትራፊክ ጥሰቶች በተፈጸሙ ጊዜ የሚጣሉ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወያይቷል፡፡ ምክር ቤቱ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

4. ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የተደረገ ለበረሃ አንበጣ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ላይም የተወያዬው ምክር ቤቱ በብድር የተገኘው ገንዘብ የበረሃ አንበጣ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ ከማስገኘቱ በተጨማሪ ከወለድ ነጻና በረዥም ጊዜ የሚከፈል በመሆኑ የብድር ስምምነቱ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

5. በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀረቡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በተመለከተም ምክር ቤቱ ተወያይቷል፡፡ አራቱ ስምምነቶች ከሩዋንዳ መንግሥት እና ከጂቡቲ ሪፐብሊክ ጋር የተደረጉ በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነቶች እና በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነቶች ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ናቸው። ምክር ቤቱ ስምምነቶቹን ተቀብሎ ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

ሌላው ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የዕቃዎች የሽያጭ ውሎች ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በዕቃዎች ዓለም አቀፍ ሽያጭ ውሎች ግንኙነት ውስጥ የሚኖረውን ተቀባይነት ከፍ የሚያደርግ እና የንግድ ግንኙነቶችን የሚያሳልጥ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁን ምክር ቤቱ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

Previous articleለደብረ ታቦር ከተማ ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ የሞባይል ሰብስቴሽን ሥራ ጀመረ።
Next articleበኢትዮጵያ ተጨማሪ 129 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፡፡