
ደሴ፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት በደቡብ ወሎ ዞን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ የዞኑ ማኅበረሰብ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ችግኞችን በመትከል ማኅበረሰቡ ሰፊ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ መንከባከብ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
በተለይም የመርሐ ግብሩ የመጨረሻ ግብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በመኾኑ ግቡን ለማሳካት የተተከሉ የደን እና የፍራፍሬ ችግኞችን ከእንስሳት እና ሰው ንክኪ ነፃ ማድረግ፣ ውኃ ማጠጣት እና መንከባከብ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በዞኑ ከሚተከሉ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው እና ለሀገር በቀል ዕጽዋት ትኩረት መሰጠቱንም ነው አቶ አሊ የተናገሩት።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ በበኩላቸው በዞኑ በአንድ ጀንበር ችግኞችን ለመትከል ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በዞኑ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የዞኑ የደን ሽፋን ከነበረበት 9 ከመቶ ወደ 14 ነጥብ 1 ከመቶ ማደጉንም አቶ አህመድ ተናግረዋል ።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደር መሐመድ አመዴ እና ወይዘሮ አሚና አሊ በየዓመቱ በክረምት ወቅት ለችግኝ ተከላ እንደሚዘጋጁ እና በዚህ ዓመትም የፍራፍሬ ችግኞችን እየተከሉ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
ከዚህ በፊት በተከሏቸው ችግኞች በተለይም በማንጎ ምርት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾን እንደቻሉም ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ የተተከሉ ችግኞችን እንደሚንከባከቡም ነው የጠቆሙት።
ዘጋቢ፦ ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን