
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተካሄደ ነው። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቀዳሚ ተግባር ኾኖ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ችግኝ መትከል ለቀጣዩ ትውልድ ሃብት ማውረስ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ድንነትን የማሸነፍ እንዱ ቁልፍ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።
ተራራዎች የናዳ እና የጎርፍ ምንጭ እንዳይኾኑ የተራራ ልማት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ እና ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት መስጠታቸውን አንስተዋል። ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተቀናጀ ተግባር እየተከወነ ነው ብለዋል።
የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በየትኛውም መስፈርት የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም፣ የተወሰነ ቡድን አጀንዳም አይደለም፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ነው፣ በሁሉም ለሁሉም የሚሠራ ተግባር ነው ብለዋል።
ኢኮኖሚውን እና አካባቢውን የጠበቀ ሀገር ጠንካራ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ ነዋሪዎች ችግኝ እንዲተክሉ እና የተተከለውን እንዲንከባከቡ ጥሪ አቅርበዋል። ታሪክ ለመሥራት፣ ነገን የተሻለን ለማድረግ እና የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ጊዜው ዛሬ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን