የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

11

ጎንደር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች፣ አባላት እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ ችግኞች የአካባቢውን የአየር ንብረት ለመጠበቅ እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል። እየጨመረ የመጣውን የሙቀት መጠን ለመቀነስ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘ መኾኑንም ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ከተተከለው ችግኝ ውስጥ 87 በመቶ መጽደቁን ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ጋር በኅብረት እየተከለ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ችግኞችን ከመትከል ባለፈ እንዲጸድቁ ከተማ አሥተዳደሩ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅርበት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌቴናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ሠራዊቱ ከሕዝብ ጋር በመኾን ለሰባት ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሲሳተፍ መቆየቱን አስታውቀዋል።

የሠራዊቱ አባላት ከመትከል ባሻገር የማጽደቅ ሥራ በትኩረት እንደሚሠሩም አብራርተዋል።

ችግኞችን በአግባቡ በመትከል ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያበቁ አንስተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገር እና ሰላምን ከመጠበቅ ባሻገር የአካባቢን አየር መጠበቅ ላይ በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በስድስት ክፍለ ከተሞች የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተከናወነ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ ቀናው አሰፋ ገልጸዋል።

የጽድቀት ምጣኔን ለመጨመር ዘላቂነት እና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማኅበረሰቡ የተከለውን ችግኝ እንዲከባከብ እና የተፋሰስ ኮሚቴ በማዋቅር የተተከሉ ችግኞች እንዲጠበቁ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከአጋር አካላት እና ድርጅቶች ጋር በመተባበር የችግኝ ተከላ ቦታዎች እንዲጠበቁ መሠራቱንም ጠቁመዋል።

ሀገር በቀል ችግኞችን በስፋት በመጠቀም ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሚውሉ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ችግኝ ሲተክሉ አሚኮ ያገኛቸው ነዋሪዎች የኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን በመረዳት ችግኞችን እየተከሉ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የተተከሉት ችግኞኝ እንዲጸድቁ ውኃ የማጠጣት እና የመንከባከብ ሥራ በቀጣይ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“እስከ ረፋዱ 5:00 ሰዓት 355 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
Next article“ችግኝ መትከል ለቀጣዩ ትውልድ ሃብት ማውረስ ነው” ርእሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ