
ደብረብርሃን፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለመጭው ትውልድ እና ለሀገር ግንባታ መሠረት እየጣለ የሚገኝ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው ያሉት የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ናቸው።
የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በአየር ንብረት ላይ ተጽዕኖ የሚያስከትል በመኾኑ ዜጎች ችግኝ የመትከል ባሕላቸውን ሊያሳድጉ ይገባል ነው ያሉት።
በአንድ ቀን ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የመጽደቅ ምጣኔን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ መርሻ አይሳነው ዛሬ እየተከናወነ በሚገኘው የአንድ ቀን ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ላይ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ችግኞች እየተተከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የአካባቢው ገፀምድር አረንጓዴ እንዲለብስ እና የሚታይ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።
እየተተከሉ የሚገኙ ችግኞች ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲኾኑ በማድረግ እንዲጸድቁ ማኅበረሰቡ ኀላፊነቱን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
በአንድ ቀን ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐግብር ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ችግኞችን ከመትከል በዘለለ ለመንከባከብ ዝግጁ መኾናቸውን ጠቁመዋል
“በመትከል ማንሠራራት” በሚል መሪ መልዕክት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የአንድ ቀን ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን