
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መሪዎች ከባሕር ዳር ነዋሪዎች ጋር በመኾን ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በድባንቄ ተራራ ላይ ችግኝ እየተከሉ ነው።
በዚሁ መርሐ ግብር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) “በመትከል መንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ሕዝቡ በንቅናቄ ወጥቶ በየአካባቢው በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
አማራ ክልል ሰላሙን አጽንቶ በአረንጓዴ ልማት ሥራ ላይ በትኩረት እየተሳተፈ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ችግኝ መትከል ትብብር፣ ዝግጁነት፣ ቅንጅት እና ሰላምን የሚፈልግ ተግባር ነው ያሉት ኀላፊው ሕዝቡ በጋራ ቁሞ ሰላሙን ማስጠበቁ እና መቀናጀቱ ለዛሬው የልማት ሥራ በር እንደከፈተ ጠቁመዋል። በቀጣይም ቢኾን ሕዝቡ ከመሪዎቹ ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ፣ ማልማት፣ ችግኝ መትከል እና የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ያለንን ክልላዊ እና ሀገራዊ ጸጋዎች በተለይም አንጓዴ ጸጋችንን ተጠቅመን የክልሉ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ እድገት እንዲሳካ እየተሠራ ነም ብለዋል ዶክተር ዘሪሁን። ለዚህም ሰላምን ማጽናት፣ አንድ ኾኖ በጋራ መቆም እና በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለልማት እና ለሰላም እንቅፉት የሚኾኑ አካሄዶችን እና አሠራሮችንም ሕግን ተከትሎ ማረም እና ማስተካከል ይበጃል ነው ያሉት።
ዶክተር ዘሪሁን በዛሬው ዕለት እርሳቸው በተሳተፉበት በባሕር ባሕር ዳተማ አሥተዳደር ድባንቄ ተራራ ላይ እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችም በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ላይ የሚሳተፉ አካላትን በሙሉ አመስግነዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደሀገር ከተጀመረ ወዲህ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የተተከሉ ችግኞች ለፍሬ በቅተው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ከተማዋ የኮሪደር ልማቷን ተከትላ ዓመቱን በሙሉ ችግኝ ስትተክል መክረሟን፣ ችግኞች እንዲጸድቁም የመንከባከብ ሥራ ሲከናወን መባጀቱን ገልጸዋል።
ባለዘንባባዋን ባሕር ዳር ከተማ ያረጁባትን የዘንባባ ተክሎች በአዲስ የመተካት እና መልኳ የበለጠ አረንጓዴ እንዲለብስ እየተሠራም ነው ብለዋል።
ዛሬ ደግሞ ከክልሉ እና ከከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች እና ከሕዝቡ ጋር በመኾን በድባንቄ ተራራ ላይ የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ አሳርፈናል ብለዋል። ከዚህ ኋፊት በከተማ አሥተዳደሩ የተተከሉ ችግኞች የመጽደቅ ምጣኔ ከ85 በመቶ በላይ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ዛሬን ጨምሮ በዚሁ ዓመት የተተከሉ ችግኞች በሙሉ ጸድቀው የታሰበውን ውጤት እንዲያስገኙም ዓመቱን በሙሉ የመንከባከብ ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
ከችግኝ መትከል በተጨማሪ የተለያዩ ተቋማት ጭምር የሚሳተፉባቸው ሰው ተኮር ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾኑም ጠቅሰዋል። በክረምት የበጎ አድርጎት ሥራዎች የአቅመ ደካሞች ቤቶች እየታደሱ ነው፤ የደም ልገሳዎች እየተካሄዱ ነው፣ የተለያዩ ሰው ተኮር ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን