
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በኮምቦልቻ ቱሉ አዳሜ ቀበሌ ቋሳር ተራራ ላይ
እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው የአረንጓዴ አሻራቸውን ያስቀመጡትና መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለረጅም ጊዜ የምንተገብረው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ አካል ነው ብለዋል።
የዓለም አንደኛው ችግር የአየር ንብረት መዛባት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ይህን የፈጠረው የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነት የተዛባ በመኾኑ ነው ብለዋል። የሰው ልጅ ተፈጥሮን ያለ አግባብ በመጠቀሙ የመጣ መዘዝ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ርሐብ እና ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ኾኗል ነው ያሉት።
ይህ በረጅም ጊዜ የመጣውን የሰው እና የተፈጥሮ የተዛባ ግንኙነት በረጅም ጊዜ ሥራ ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ ልዩ ትኩረት በመስጠት አስደማሚ ሥራ እየሠራች መኾኗን ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተፈጥሮን ለሰው ልጅ የማመቻቸት ተግባር ነው ብለዋል።
ዛሬ የሚተከሉ ችግኞች ለነገ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያላቸው፣ የሀገርን እና የቤተሰብን ገቢ የሚያሳድጉ ናቸው ነው ያሉት። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በምግብ ራስን ለመቻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላውም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ስትፈተን መቆየቱንም ገልጸዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። ሁሉም ሀገራት በአረንጓዴ አሻራ ከተሳተፉ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል እንደሚቻል ነው የገለጹት።
በአማራ ክልል በሁሉም ዞኖችና ከተማ አሥተዳደሮች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ እየተሳተፉ መኾናቸውን አስታውቀዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አንዱ የኢኮኖሚ ልማት ሥራችን አድርገን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!