“የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሚሊዮኖችን ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ትርጉም አለው” የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ

8

የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመላ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው። ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሻራቸውን እያሳረፉ ነው።

በለገጣፎ አካባቢ የአረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉት
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊ ካሳ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለትውልድ ከሚተርፉ ትልልቅ ሥራዎች መካከል አንደኛው ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ልምላሜ የመለሰ ብቻ ሳይኾን ሚሊዮኖችን ለአንድ ዓላማ በየጊዜው እንዲሰለፉ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።

ከቱሪዝም ቤተሰቦች ጋር እየተከሉ መኾናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከቱሪዝም ዘርፉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ገልጸዋል።

ጥብቅ ደኖች እና ብሔራዊ ፓርኮች ያለ አረንጓዴ ልማት መቀጠል አይችሉም ነው ያሉት። ከተፈጥሮ ጋር የተሳሳረ እና የተጣጣመ የቱሪዝም ዘርፍ መመስረት የሚቻለው እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን መሥራት ሲቻል ነው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በራሱ የሚነገር ታሪክ ነው፣ እንደ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎች ሁሉ የአረንጓዴ አሻራችንም ወደ ፊት ይጎበኛል ነው ያሉት። ጽኑ ባሕል ኾኖ ለትውልድ እስኪቀጥል ድረስ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ ልምላሜ ብቻ አይደለም፣ ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ ነው፣ ለተፈጥሮም እየቆምን ነው፣ ተፈጥሮ ደግሞ መልሶ ይክሰናል ነው ያሉት። በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን ግብ ማሳካት እንደምትችል አንዱ ማሳያ ነው” የግብርና ሚኒስቴር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)
Next article“በረጅም ጊዜ የመጣውን የሰው እና የተፈጥሮ የተዛባ ግንኙነት በረጅም ጊዜ ሥራ ማስተካከል ያስፈልጋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ