
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው በንቅናቄ ወጥተው በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ኢትዮጵያን አረንጓዴ እያለበሱ ነው። መሪዎች ከሕዝብ ጋር እየተቀናጁ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች አረንጎዴ አሻራቸውን እያሳረፉ ነው።
ይህንን አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) የሀገሪቱ ሕዝቦች እና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት ወጥተው በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያ ያሰበችውን እየፈጸሙ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከእቅድ በላይ ተፈጽሟል፣ በቀደሙት ዓመታትም ከታቀደው በላይ ተተክሏል ነው ያሉት። “አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን ግብ ማሳካት እንደምትችል አንዱ ማሳያ ነው” ብለዋል።
“አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከልም በላይ የኢትዮጵያዊ የአንድነት እና የትብብር ምልክት ነው” ያሉት ዶክተር ግርማ በሰባተኛው ዓመትም 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ሕዝቡ እየተሳተፈ ስለመኾኑን አንስተዋል።
የችግኝ መትከያ ቦታዎች እና የችግኙ ዓይነት በሳይንሳዊ ዘዴ ቀድሞ የተለየ ስለመኾኑም ገልጸዋል። በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄደውን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ሂደት ለመከታተልም ዘመናዊ የኾነ የኹነት መከታተያ ክፍል ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፋት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች በአጠቃላይ ከ40 ቢሊዮን ችግኞችን መትከሏን አስታውሰዋል።
በ2018 ዓ.ም ከሚተከለው ጋር ተደምሮ የሀገሪቱ እስከ 2018 ዓ.ም 50 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ ይሳካል ነው ያሉት። በተለይም የዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሕዝቡም ቀድሞ የተዘጋጀበት እና በላቀ ንቅናቄ እየተፈጸመ ያለ መኾኑ ለእቅዱ መሳካት አመላካች ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!