ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መልበስ መዘንጋት እንደሌለበት የዓለም ጤና ድርጅት አሳሰበ፡፡

190

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) የዓለም ጤና ድርጅት የተሻሻለውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም መመሪያ ይፋ አድርጓል፡፡

የኮሮናቫይረስ ስርጭት አሳሳቢነቱ መቀጠሉን ተከትሎን የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ ቀደም ያሰቀመጠውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም መመሪያ አሻሽሏል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶክተር) እንደገለጹት በአዲሱ መመሪያ መሠረት ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መልበስ መዘንጋት የለበትም፡፡

የኮሮናቫይረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ በተሠራጨባቸው አካባቢዎች የሚሠሩ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች ለሕክምና ባለሙያዎች የተዘጋጁ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ሊጠቀሙ እንደሚገባም የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል፡፡ በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች የሕክምና ባለሙያዎችን ጭምብል በጠቀም ያለባቸው በቀጥታ የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን የሚንከባከቡ ሐኪሞች ብቻ አለመሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡

መሸፈኛዎቹ ከአፍና አፍንጫ የሚወጡ ነጠብጣቦች ወደ ጤነኛ ሰዎች እንዳይገቡ ለማገድ ስለሚረዱ አንዳንድ ሀገራት ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ጭምብል እንዲለበስ ቀድመው ማሳሰባቸውንም ዶክተር ቴድሮስ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ቫይረሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ በተሰራጨባቸው ቦታዎች እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይቻልበት ሁኔታ ማስክ መጠቀም ተገቢ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይ ዕድሜያቸው 60 እና ከዚያ በላይ የሆኑት ወይም የጤና እክል ያለባቸው ደግሞ ለሕክምና የሚያገለግሉ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን እንዲለብሱ መክረዋል፡፡

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን መልበስ አንድ የመከላከያ መንገድ መሆኑን ያስታዎሱት ዶክተር ቴድሮስ አካላዊ ርቀትን እና የእጅ ንጽሕናን መጠበቅ ላይ መዘናጋት እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡

የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለማችን 6 ሚሊዮን 852 ሺህ 838 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፤ 398 ሺህ 286 ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ 3 ሚሊዮን 352 ሺህ 731 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡

ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ

በኪሩቤል ተሾመ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleማይክል ጆርዳን ዘረኝነትን ለመዋጋት 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መደበ፡፡
Next articleየኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ የሚመልሱ እንዲሆኑ ርእሰ መሥተዳደሩ አሳሰቡ።