
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በከተማዋ ካዛንችስ አካባቢ ተገኝተው በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።
ምክትል ከንቲባው እንዳሉት በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ቀደም ብለው የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች እና ችግኞች ለአንድ ጀንበር ተከላ ተዘጋጅተዋል።
ዛሬ ላይም ከንጋቱ ጀምሮ ሁሉም የከተማዋ መሪዎች ከነዋሪዎች ጋር በመውጣት አሻራቸውን እያሳረፉ ነው ብለዋል።
የወንዝ ዳርቻዎችን ማልማት እና በዚያው ችግኝ መትከል በተለይም በክረምት ይጠረግ የነበረውን አፈር ማስቀረት ተችሏል ነው ያሉት።
የተተከሉ ችግኞችም ለወንዝ ዳርቻ ልማቱ የበለጠ ውበት የሚሰጡ ስለመኾኑ ምክትል ከንቲባው አመላክተዋል።
ችግኞች አፈርን እንዲይዙ እና የአካባቢውን ውበት እንዲጠብቁ ታስቦ ከእንጦጦ ጀምሮ በየወንዞች ዳርቻ እየተተከሉ ነውም ብለዋል።
በየአካባቢውም ለምግብነት የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎች እየተተከሉ እንደኾነም ጠቁመዋል።
በጥራት እና በአይነት የተሻሉ ችግኞች ተዘጋጅተዋል፣ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችም በንቅናቄ ወጥተው ችግኞችን እየተከሉ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን