
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጋምቤላ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በክልሉ የሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ ጥበቃን ከማጠናከር ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ለትውልዶች የተመቸች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው ብለዋል። ላለፉት ዓመታት በክልሉ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ፍሬ ማየታቸውን ገልጸዋል። የተተከሉት የፍራፍሬ ዛፎች ምርት መስጠት መጀመራቸውንም ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናን በማሳደግ፣ የቤተሰብ ገቢን በመጨመር እና የክልሉን አረንጓዴነት ከፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት። ውጤቶችን ለማስቀጠል የሀገራዊ ንቅናቄው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ የፍራፍሬ እና የችግኝ ዛፎችን እንዲተክልም ጥሪ አቅርበዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በማንሠራራት፣ ከድህነት በመላቀቅ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ባሕል ኾኖ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብ ሕይወቱ ከተፈጥሮ ሃብት ጋር የተቆራኘ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሯ ዛሬ የሚተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከቡም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን