የ2017 ዓ.ም የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ መልዕክት፦

33

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ይስጥልን እንደምን አደራችሁ!

በቅድሚያ መላው ኢትዮጵያውያንን እንኳን ለዚህ ዐዲስ ታሪክ ለምናስመዘግብበት ልዩ ቀን አደረሰን አደረሳችሁ! የዛሬዋ ዕለት ኢትዮጵያውያን የመቻል ዐቅማችንን ደግመን ደጋግመን ለዓለም የምናሳይባት ልዩ ቀን ናት! የራሳችንን ክብረ ወሰን ራሳችን ለማሻሻል በአንድ ጀምበር
700 ሚሊዮን ችግኞችን የምንተክልባት ቀን ናትና!

ኢትዮጵያውያን ባለፉት 6 ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም የአካባቢ ጥበቃ ጥረት ከፍተኛ ሚና ተወጥተናል። በአንድ ጀምበር በርካታ ሚሊዮን ችግኞችን በመትከልም በየዓመቱ የራሳችንን ክብረ ወሰን እያሻሻልን ዛሬ 7ኛ ዓመት ላይ ደርሰናል። ዛሬ
በ7ኛ ዓመታችን ደግሞ 700 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ዐዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመጻፍ ተዘጋጅተናል።

“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሐሳብ በዚህ ክረምት 7.5 ቢሊዮን የደን፣ የመኖ እና የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል ጀምረናል። ዛሬ በዕለተ ኀሙስ ሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የራሳችንን ክብረ
ወሰን ከፍ እናደርገዋለን። በኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ሌላ ዐዲስ ታሪክ እንጽፋለን።

ባለፈዉ ዓመት በአንድ ጀምበር 617 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል የቀዳሚውን ዓመት መጠን አሻሽለናል፤ ዘንድሮም የራሳችንን ክብረ ወሰን ለማሻሻል 700 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን ለመትከል ከሕፃናት እስከ ሀገር ባለውለታ አረጋውያን፤ ከሃይማኖት አባቶች እስከ ምዕመናን፤ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርሶ እና አርብቶ አደሮች፣ የጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እና ሌሎችም የፀጥታ አካላት፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ የሚገኙ ኹሉ አረንጓዴ ዐሻራችንን
ለማኖር ተዘጋጅተናል። የዚህ ታሪካዊ ተግባር ተሳታፊ በመኾናችንም ኩራት ይሰማናል።

ችግኞችን የምንተክለዉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራችንን ለማጠናከር፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ በላባችን እና በጥሪታችን የገነባናቸዉን ግድቦቻችንን ከደለል ለመጠበቅ፣ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ፣ የእንስሳት መኖን በበቂ ለማምረት እና ኢትዮጵያን
አረንጓዴ ለማልበስ ነው። የዓለም ስጋት እየኾነ የመጣዉን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም አብነት ለመኾንም ነው።

“በመትከል ማንሰራራት” የሚል መሪ ቃል ሲመረጥ ሃገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታና መጻዒ ተስፋ በማየት ነው። በዚህ ዓመት መንግስት ህዝብን በማስተባበር ባከናወናቸው ሰፋፊ የልማት ስራዎች ሃገራችንን ወደ ቀጣዩ የእድገት ጎዳና እንድትገባ የሚያስችሉ መደላድሎች፣ ለላቀ ስኬት የሚያስፈነጥሩ መስፈንጠሪያዎች ተሳክተዋል። የዐበይት ፕሮጀክቶች ፍጻሜ፣ የኤስክፖርት ግኝታችን፣ የሥራ እድል ፈጠራችን በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸማችን እና የተቋማት ግንባታችን የማንሰራራት ብስራቶቻችን ናቸው። ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞችም ሆነ እስካሁን ያደረግናቸው የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎቻችን በአንድ በኩል እነዚህ
ግኝቶቻችንን የበለጠ የሚያሰፉ፣ በሌላ በኩልም ለቀጣዩ ትውልድ ዘላቂና አዛላቂ ልማትን ለመተው የሚያስችል ነው።

ዛሬ በሚኖረን ቆይታ በመላ ሃገራችን አግሮ ኢኮሎጂው በፈቀደባቸው ቦታዎች በሙሉ ተከላዎች ይከናወናሉ። እነዚህን ተከላዎች በየጣቢያው የተመደቡ የግብርና ባለሞያዎች መረጃዎችን በመላክ በማዕከል የሚጠመር ሲሆን ኹነቱን ደግሞ በየቦታው የተሰማሩ የሚዲያ
ባለሞያዎች ያደርሱልናል። ከዚህ ከጊዜያዊ የማስተባበሪያ ጣቢያ የተጠመረው ሃገራዊ አሃዝ የሚቀርብ ሲሆን በየተወሰነ ሰዓት ልዩነት አጫጭር ማብራሪያዎችን እየሰጠናችሁ አብረናችሁ እንውላለን።

ስለዚህ ዛሬ ኢትዮጵያውያን በመላው ሀገሪቱ የተዘጋጁ ችግኞችን በተዘጋጁት ቦታዎች ተገኝተን በመትከል ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል። ይህ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ጥሪ በዋዛ ሊታለፍ የማይገባ ልዩ የሕይወት አጋጣሚ ነው፤ ኢትዮጵያን ወደላቀ ከፍታ የማውጣት፤ ለእናት ሀገር ትንሽ አስተዋጽኦ የማበርከት ጅማሮ፣ ስምን ለቀጣዩ ትውልድ በኩራት የማውረስ … ጉዳይ ነውና። በመኾኑም የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ከጧቱ 12፡00 ጀምሮ እየተከናወነ ስለሚገኝ ኹላችንም በየአቅራቢያችን በተዘጋጁ
ቦታዎች በመገኘት ዐሻራችንን እንድናኖር መንግሥት ጥሪዉን ያቀርባል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጋራ እናሳከዋለን” ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Next article” በጋራ እናሳካው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)