
በዓባይ ወንዝ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ ቴክኒካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች እና ወቅታዊ የድርድር አላባውያን ላይ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ስለታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ነባራዊ ሁኔታ እና አሁናዊ የድርድር ሂደት፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በዓባይ ጉዳይ ላይ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዙሪያ ያሉ ዓለም አቀፍ ሕጎች እና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱባቸው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በውይይቱ ይተነተናሉ። እነዚህን እና ተያያዥነት ያላቸው ታሪካዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማንሳትም የኢትዮጵያን የተጠቃሚነት መንገዶች የሚያመላክቱ ምክረ ሐሳቦች ይቀርባሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሕግ አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ኃላፊዎች በውይይቱ ተገኝተዋል። የክልል የሥራ ኃላፊዎች እና ከልዩ ልዩ ተቋማት የተውጣጡ ሰዎችም ተገኝተዋል።
ውይይቱ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲው ብሉ ናይል የምርምር ማዕከልና የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ትብብር የተዘጋጀ መድረክ ነው።
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ