“ጀምረናል እንጨርሳለን፣ ተልመናል እናሳካለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

18

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት ችግኝ ተክለዋል።

በኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር ከማለዳ ጀምሮ መካሄድ ጀምሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ቀዳማዊት እመቤቷም በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ ነው አሻራቸውን ያሳረፉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት “የጀመርነው እንቅስቃሴ ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል” ብለዋል። በሰባተኛ ዓመታችን በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኝ እንተክላለን ነው ያሉት።

በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ትልቅ እምርታ እና በዓለም ትልቁ የአንድ ቀን ተከላ ውጤት ነው ብለዋል።

በዚህ ዓመት ወደ 8 ቢሊዮን ገደማ ችግኞች እንደሚተከሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያን ካሳካን በድምሩ 48 ቢሊዮን ችግኞች እንተክላለን ነው ያሉት።

50 ቢሊዮን ችግኝ የምትከል ዕቅድ እንዳለ እና በሚቀጥለው ዓመት ከሚተከለው ጋር ከ50 ቢሊዮን እንደሚሻገር ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ታላላቅ ነገር አስባ እና ልጆቿን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ለእኛም ለዓለምም ማሳያ ነው ብለዋል።

ማንም ሀገር እንደዚህ አላደረገም፣ እኛ ይሄን ያደረግነው ሃብታም ስለኾንን አይደለም፣ ሀብታም ልብ ያላቸው ልጆች ስላሉን ነው፣ ዜጎቻችን ልባቸው ሃብታም፣ አርቆ ማየትን፣ የጋራ ራዕይ መሰነቅን፣ አብሮ መሥራትን፣ በልፋት በድካም ውስጥ ትርፋማ መኾንን ማመን ስለቻሉ ነው ብለዋል።

በዚህ አስደናቂ ሥራ ኢትዮጵያ ያሰበችውን ማሳካት መቻሏን ገልጸዋል። ይህ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ የኢትዮጵያዊያን የትልቅ አሻራ አካል ነው ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ ማትረፋቸውንም ተናግረዋል።

የችግር እና የድህነት ምልክት የኾነችው ኢትዮጵያ መልኳ እየተቀየረ መኾኑንም ገልጸዋል ። ይህን ያደረግነው ለፍተን ነው ብለዋል። ኢትዮጵያን ከችግር ማውጣት የዜጎቿ ኀላፊነት መኾኑንም ተናግረዋል።

በአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት አሻራቸውን ማሳረፋቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተከሉ እንዲተክሉ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ታሪክ ነው፣ ነገ አይደገምም፣ የታሪክ አካል አንዲኾኑ ኢትዮጵያውያን መትከል አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያን እንዲያለብሱ፣ ቀኑ የውጤት የደስታ ቀን፣ የስኬት ቀን እንዲኾን ተመኝተዋል። ይህ እንዲሳካ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ጀምረናል እንጨርሳለን፣ ተልመናል እናሳካለን፣ ደሃ ነበርን እንበለጽጋለን፣ የኢትዮጵያ መልክ እና ታሪክ ይቀየራል፣ የታሪክ እጥፋት አካል መኾን መታደል ስለኾነ እንበርታ ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በፍኖተ ሰላም ከተማ ተጀመረ።
Next articleበምዕራብ ጎንደር ዞን የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተጀምሯል።