
አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርምር ግምገማ እና ዓመታዊውን የምርምር ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሕዝቡን የጤና ስጋቶች ሊመልስ በሚችል መልኩ ተቋማዊ ኀላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል ብለዋል።
የጤና ስጋቶችን ቀድሞ በመተንበይ እና በመከላከል እረገድም አቅም የሚኾኑ ውጤታማ የምርምር ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
ዶክተር መሳይ በኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ባለፉት ዓመታት ውሳኔዎች መረጃ ላይ የተመረኮዙ እንዲኾኑ ኢንስቲትዩቱን የሚደግፉ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥናት እና ምርምሮችን ማድረግ ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው የሚሻሻሉ ፖሊሲዎች ውጤታማ እንዲኾኑ ምርምር ላይ መሠረት አድርገው መዘጋጀት አለባቸውም ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር የስትራቴጂ ዕቅዶቹን ለማቀድ የኢንስቲትዩቱን መረጃ በግብዓትነት እንደሚጠቅምም ገልጸዋል።
ለአብነትም ወረርሽኞች፣ ሥርዓተ ምግብ እና የባሕል ሕክምና ላይ የተሠሩ ምርምሮች እና የተገኙ ውጤቶች እንደሀገር አቅም የተፈጠረባቸው መኾናቸውን አስገንዝበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ወካይ በሚባሉ የሀገሪቱ አካባቢ ላይ የተሠሩ ዓመታዊ የጥናት እና ምርምር ውጤቶች ይፋ ይኾናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ ፦ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን