የ“ኃይሌ ሚናስ አካዳሚ” አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ 85 በመቶ መድረሱ ተገለጸ፡፡

462

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ በ12 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጭ እየተገነባ የሚገኘው “ኃይሌ ሚናስ አካዳሚ” አዳሪ ትምህርት ቤት 85 ከመቶ የግንባታ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡

አማራ የክልልና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤቱ “ኢትዮጵያ ኢዱኬሽን ኢንሼቲቭ” የተሰኘ ድርጅት መስራችና ባለቤት በሆኑት ርብቃ ኃይሌ እና ጆን ማናፍ በተባሉ በጎ አድራጊ ግለሰብ ነው እየተገነባ የሚገኘው፡፡ ሥራው ታህሳስ 2011 ዓ.ም ነበር የተጀመረው፤ ለማጠናቀቅ የታቀደውም ነሃሴ 2012 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ኃላፊ አቶ ተስፋየ ክፍሌ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ለኢትዮጵያ ሞዴል እንዲሆን ታስቦ እየተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያሚያመጡ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በውድድር የሚገቡበት እንደሚሆንም ነው ያስታወቁት፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤቱ 14 የመማሪያ እና 8 የቤተ ሙከራ ክፍሎች፣ 4 የተማሪዎች መኖሪያ ሕንጻዎች እና 8 መምህራን መኖሪያ ህንጻዎችን ጨምሮ የጤና ማዕከል፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የስፖርት ሜዳ፣ የአካል በቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ አዳራሽ (ጅምናዚየም) እንዲሁም የአረንጓዴ ቦታዎችን ያካተተ መሆኑም ታውቋል፡፡ በዚህ ጊዜ ያለበት የግንባታ አፈጻጸም 85 ከመቶ መሆኑንና ቀጣይ የሚቀሩት የውስጥ ለውስጥ መንገድና ሌሎች የማጠቃለያ ሥራዎች እንደሆኑ የፕሮጀክቱ ኃላፊ ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የግንባታ ሂደቱን በተወሰነ ደረጃ ተጽዕኖ እንደፈጠረበት የተናገሩት አቶ ተስፋየ በቀጣይ ዓመት ለማስተማሪያነት እንዲደርስ የማድረግ ዕድል መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ የሚቀጠሩ መምህራንም ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት የውጭ ሃገራት፣ ከ60 እስከ 70 በመቶዎቹ ደግሞ የሃገር ውስጥ እንደሚሆኑ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደስታ አንዳርጌ በአይነቱ ልዩ የሆነውን ፕሮጀክት እየገነቡ ያሉትን በጎ አሳቢ ግለሰቦች አመስግነዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ለአዳሪ ትምህርት ቤቱ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

“ኃይሌ ሚናስ አካዳሚ” አዳሪ ትምህርት በስምንት ሄክታር መሬት ላይ ነው እየተገነባ የሚገኘው፡፡

ዘጋቢ፡- ይርጋዓለም አስማማው-ከደብረ ብርሃን

Previous articleዛሬ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣይ ሥራዎች ግንዛቤ መፍጠሪያ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ዓለማቀፍ ወንዞች አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሔደ ነው።