በማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ ዋነኛው ትኩረት ነው።

12

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ እፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ አካሂዷል።

የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ረዳት ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ማረሚያ ቤቶች መፈተናቸውን ገልጸዋል። በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ላይም ጉዳት መድረሱን ነው የገለጹት።

ይሁን እንጅ ከሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት በተሠራው ሥራ በተቋማቱ ላይ የከፋ ችግር እንዳይደርስ ተደርጓል ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም በጸጥታ ጉዳይ የወደሙ 13 የሚኾኑ ማረሚያ ቤቶችን ማኅበረሰቡን በማስተባበር እና በራስ አቅም በማጠናከር ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት። ከባለፉት ጊዜያት በተሻለ መንገድ በታራሚዎች ሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ትኩረት ተሠጥቶ መሠራቱን ነው የገለጹት።

የማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጭምር ክትትል መደረጉንም ገልጸዋል። ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል የሪፎርም ሥራ ማስፈጸሚያ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።

ታራሚዎች መደበኛ እና የሙያ ትምህርት እንዲማሩ እና በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ መደረጉን አንስተዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ታሪኩ ዳኘ በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ ማረሚያ ቤቶች በውጭ ቡድኖች እና በታራሚዎች ጭምር ተፈትነው እንደነበር ገልጸዋል።

ከፈረሱ ማረሚያ ቤቶች የወጡ ዜጎች የአካባቢውን ሰላም የማወክ፣ የመዝረፍ እና የማገት ተግባር ላይ ተሠማርተው መታየቱን ገልጸዋል። ማረሚያ ቤቶች የሚታረሙ ዜጎች የሚገኙባቸው ተቋማት በመኾናቸው ማኅበረሰቡ ሊጠብቃቸው ይገባል ብለዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ፈንታው ደሳለኝ ባለፉት ዓመታት በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

በጉዳቱ ምክንያት ተበትነው የነበሩ ታራሚዎችን በማኅበረሰቡ ጥቆማ፣ በጽጥታ ኀይሉ ክትትል፣ በማረሚያ ቤቶች ጥሪ እና በሕግ ታራሚዎች ፈቃደኝነት ወደ ማረሚያ ቤቶች እንዲመለሱ ተደርጓል ነው ያሉት።

የወደሙ ተቋማትንም መልሶ የመግንባት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ የላሊበላ ማረሚያ ቤት በሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በተከታታይ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ነው የገለጹት።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ማረሚያ ቤት መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሹመት ሞላ ባለፉት ዓመታት ማረሚያ ቤቶች ቢፈተኑም ከሌሎች የጸጥታ አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት የመጠበቅ፣ የማረም እና የማነጽ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሠጥቶ ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም የማረሚያ ቤቶችን ሕግ የማስከበር፣ የጥበቃ እና ደኅንነት ተግባርን ማጠናከር እና በኮሚሽኑ የተያዙ የዲጅታላይዜሽን ሥራ ማስፋት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የተሰጠን ዕውቅና በሙያችን የልኅቀት ማዕከል ኾነን ሕዝብን እንድናገለግል አደራም ጭምር ነው” ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ
Next articleየጤና ስጋቶችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ የምርምር ሥራዎች ተሠርተዋል።