“የተሰጠን ዕውቅና በሙያችን የልኅቀት ማዕከል ኾነን ሕዝብን እንድናገለግል አደራም ጭምር ነው” ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ

11

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ለርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እና ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ዕውቅና መስጠቱ ይታወሳል።

የክልሉ ሕዝብ ችግር ላይ በወደቀበት ጊዜ ሁሉ አሚኮ እና ባለሙያዎቹ በጽናት በመቆም እና ለሕዝብ የሚበጁ አሻጋሪ መረጃዎችን እና አስታራቂ ሃሳቦችን በማድረሳቸው ነው ምክር ቤቱ ለአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ዕውቅና የሰጠው።

ይህንን ከሕዝብ የተሰጠ ዕውቅና ተከትሎ በቀጣይም ሕዝብን የበለጠ ለማገልገል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ የአሚኮ ባለሙያዎች እና መሪዎች ተወያይተዋል።

ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ “የተሸለሙት አሚኮ እና የአሚኮ ሠራተኞች ናቸው፤ ዕውቅናው ለሕዝብ ሲሉ በችግር ውስጥ እያለፉ እና ጨለማ ሳይበግራቸው ለታተሩ ጋዜጠኞች እና ባለሙያዎች ውጤት ነው” ብለዋል።

አሚኮ ፈተና የበለጠ የሚያጸናቸው፣ ችግር የበለጠ የሚያጠነክራቸው ግሩም ባለሙያዎች አሉት፤ እነዚህን ባለሙያዎች በመምራት ለስኬት መሥራት ያስደስታል ነው ያሉት። የተገኘው ዕውቅናም የጋራ ውጤት ነው ብለዋል።

“ሕዝብ ዕውቅና የሰጠን ስንሠራ ፈተና ስለሌለ አይደለም፤ ይልቁንም በፈተናዎች ሁሉ የማንወድቅ እና ሕዝብን እያሰብን በጽናት የምንሠራ በመኾናችን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በችግር ውስጥ ኾነን ለሕዝብ ይበጃል ያልነውን ሁሉ በመሥራታችን የተሰጠን ዕውቅና በቀጣይ የመገናኛ ብዙኅን የልኅቀት ማዕከል ኾነን ሕዝብን እንድናገለግል አደራም ጭምር ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በጋራ፣ በመተሳሰብ እና ሕዝብን በማክበር በመሥራት የአሚኮን ተቋማዊ ከፍታ እና ሕዝባዊ አገልግሎት ከዚህ በላይ ማሳደግ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ አሚኮ ከዚህ በፊትም በርካታ ሽልማት አግኝቷል፤ ትላንት በምክር ቤቱ የተሰጠው ሽልማት ግን ከሽልማቶች ሁሉ ልዩ ነው ብለዋል። ምክንያቱም አሚኮን የሸለመው የሕዝብ ወኪል የኾነው ምክር ቤት ወይም ያገለገለው ሕዝብ በመኾኑ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሌት ከቀን በብርታት በመሥራቱ፣ ሌሎችም መሪዎች ተግተው በመሥራታቸው እና መላው የአሚኮ ቤተሰቦች አንድ ኾነው እና ተናብበው በመሥራታቸው የተገኘ ውጤት ስለመኾኑም አብራርተዋል።

ሽልማቱ ሁለት መልዕክት አለው ያሉት አቶ ግዛቸው የመጀመሪያው አሚኮ ለክልሉ ሰላም እና ልማት በማሰብ በችግር ውስጥ ኾኖም ሕዝቡን በትጋት ሲያገለግል መቆየቱን የሚገልጽ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ የክልሉ ሕዝብ ከገጠመው የግጭት እና ድህነት አዙሪት በዘላቂነት እንዲወጣ የአሚኮ የወደፊት ሚና ከፍተኛ መኾኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

አሚኮ ከአማራ ክልል እና ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካ ጭምር አገልጋይ ሚዲያ እንዲኾን በላቀ ትጋት መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

ሌሎችም የአሚኮ መሪዎች እንዳሉት አሚኮ በተቋም ግንባታ ሂደቱ የባለሙያዎቹን አመለካከት እና ክህሎት በሚገባ እየቀረጸ እና አገልጋይነቱን የበለጠ እያሰፋ መጓዙ ለውጤት እና ለዕውቅና አብቅቶታል።

አሚኮ ሙያን እና የሙያን ሥነ ምግባር መሠረት አድርጎ የቆመ፤ የሚገጥሙትን ችግሮች ሁሉ በመርህ እና በጽናት ላይ ቆሞ እያለፈ የሚሠራ ሚዲያ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

አሚኮ እና መሪዎች ያገኙት ዕውቅና መላውን ባለሙያ “ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን” በማለት እና በማቀናጀት ለተሠራው ሥራ ውጤት ስለመኾኑም የአሚኮ ጋዜጠኞች ገልጸዋል።

አሚኮ ቀደም ሲልም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጭምር ዕውቅና ተሰጥቶታል፤ አሁን የተሰጠው ዕውቅናም መሪዎች እና ባለሙያዎች በጋራ እና በጽናት በመሥራታቸው የተገኘ ስለመኾኑም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

የተሰጠው ዕውቅና የአሚኮን ባለሙያዎች ለላቀ ውጤት የሚያነሳሳ እና ለሙያዊ ጉዞ የቤት ሥራ ስለመኾኑም ተነግሯል። በሕዝብ የተሰጠው ዕውቅና ያልተሠሩ እና ያልታዩ ጉዳዮች እንዲፈለጉ፣ ባለሙያዎችም ዕውቀት እና ክህሎታቸውን የበለጠ በማዳበር ሕዝብን በልኅቀት እንዲያገለግሉ መነሻ ይኾናል ነው ያሉት ጋዜጠኞቹ።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጣና ነሽ “፪” ቡሬ ከተማ ደረሰች።
Next articleበማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ ዋነኛው ትኩረት ነው።