
ገንዳውኃ፡ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ከ5 ሺህ 80 ኩንታል በላይ እጣን እና ሙጫ ምርት መሠብሠብ መቻሉን የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
የዞኑ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የአካባቢ የሕግ ተከባሪነት እና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ ሀብታሙ አድጎ ከእጣን እና ሙጫ ምርቱም ከ108 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘት መቻሉን ነው ያብራሩት።
ከፍተኛ የኾነ የእጣን እና ሙጫ ምርት የሚያስገኝ የደን ሃብት በአካባቢው መኖሩንም ጠቁመዋል።
በአካባቢው ከ760ሺህ ሄክታር በላይ የሚጠጋ የደን ሽፋን ውስጥ ከ234ሺህ ሄክታር በላይ የእጣን እና ሙጫ ዛፍ መኖሩን ቡድን መሪው አብራርተዋል።
በሥራ እንቅስቃሴው 45 ማኅበራት እና ባለሃብቶች በወረዳ የደን ግብረ ኀይል ቢፀድቅላቸውም በክልል ደረጃ ለ17 አምራቾች ብቻ ሕጋዊ ኾነው ማምረት እንዲችሉ የተፈቀደላቸው መኾኑን ተናግረዋል።
ከ700 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች በቋሚ እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መኾኑንም ጠቁመዋል።
አምራቾች ካገኙት ገቢ ለመንግሥት የሮያሊቲ ክፍያ ከ21ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘታቸውንም ቡድን መሪው አብራርተዋል።
በዞኑ ቋራ እና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች የተመረተው ምርት በአምራቾች ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ ቢኾንም በላኪዎች አማካኝነት ወደ ውጭ በመላክ ለምንዛሬ አገልግሎት የሚውል መኾኑን አስገንዝበዋል።
በመተማ ወረዳ ሌንጫ ቀበሌ አዲስ ሕይወት የኅብረት ሥራ ማኅበር ሠብሣቢ በየነ ውቤ በዚህ ዓመት ከ220 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
ማኅበሩ 60 አባላት እንዳለው ጠቅሰው ለኩንታል 53ሺህ ብር በጨረታ በመሸጥ ከ12ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
የእጣን ዛፉ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ በማምረት ሂደት እና ከምርት በኋላ ተገቢውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉም አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን