
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሩሲያ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው የካምቻትካ የባሕር ወሽመጥ በሬክተር ስኬል 8 ነጥብ 8 የኾነ ርዕደ መሬት መከሰቱን በቢሲ ዘግቧል።
ይህን ተከትሎ በጃፓን፣ በሀዋይ እና በአሜሪካ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻዎች የሱናሜ ሥጋት ተፈጥሯል። በእነዚህ አካባቢዎ ያሉ ነዋሪዎች ከስፍራው ርቀው ከፍታማ ቦታዎች ላይ እንዲቆዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ቢቢሲ በዘገባው አስታውቋል።
በተጨማሪም የተለያየ መጠን ያለው ማዕበል በቻይና፣ ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኖዢያ፣ ጉዋም፣ ፔሩ እና በኢኳዶር ጋላፓጎስ ደሴቶች በመታየቱ ሥጋቱ እየጨመረ መሄዱ ተጠቁሟል።
በካምቻትካ ከ3 እስከ 4 ሜትር ከፍታ ያለው የሱናሜ ማዕበል መከሰቱ ሲገለጽ በሰሜናዊ የጃፓን ሆካይዶ ከተማ ደግሞ 30 ሴንቲ ሜትር ከፍታ ያለው ማዕበል ታይቶባታል።
የሀዋይ ግዛት አሥተዳደር ጆሽ ግሪን ዜጎች ከአካባቢው እንዲርቁ የሚተላለፍላቸውን ትእዛዝ እንዲያከብሩ እና እንዲረጋጉ ጠይቀዋል። የአሜሪው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም አሜሪካውያን ለሱናሜ ማስጠንቀቂያዎች ንቁ ኾነው እንዲጠብቁ መክረዋል።
ታስ የተባለው የሩሲያ የዜና ወኪል እንደዘገበው በካምቻትካ ርዕደ መሬት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን እና ሌላም ርዕደ መሬት ሊከሰት እንደሚችል ዘግቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን