የአልማ አቅም ሕዝቡ ነው።

21

ደሴ፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከአማራ ልማት ማኅበር አልማ ጋር ከዩኒሴፍ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ደጋን ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ለእናቶች እና ሕጻናት ሕክምና መስጫ በሰባት ሚሊዮን ብር ያስገነባው ማዕከል ሥራ ጀምሯል።

የደጋን ጤና አጠባበቅ ኀላፊ ኪሩቤል ደምሴ በጤና ጣቢያው ለእናቶች ይሰጥ በነበረው አገልግሎት በወሊድ ጊዜ የማቆያ ክፍል ጥበት፣ የአልጋ እጥረት እና የሕክምና መስጫ ቁሳቁስ ችግሮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ሕንጻ ይህንን ችግር የቀረፈ መኾኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ 800 ሺህ ብር በሚገመት ገንዘብ የሕክምና ቁሳቁስ ተሟልቶለታል ብለዋል።

ጤና ጣቢያው ከደጋን ከተማ በተጨማሪ ለገርባ እና ሌሎች በዙሪያው ላሉ ቀበሌዎች አገልግሎት የሚሰጥ ሲኾን በወር ከ70 በላይ የሚኾኑ ወላዶችን እስካሁን እያስተናገደ እንደኾነም አስረድተዋል።

የእናቶች እና ሕጻናት ጤናን ለማሻሻል በዞኑ በርካታ ሥራዎች እየከናወኑ መኾናቸውን የገለጹት የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው በለጠ የጤና መሠረተ ልማትን መገንባት መቻሉን አንስተዋል።

በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ባሉ አብዛኛዎቹ ጤና ጣቢያዎች ላይ የአልትራሳውንድ እና የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በዚህም የእናቶችን ሞት እና እንግልት መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።

ዛሬ የተመረቀው የእናቶች እና ሕጻናት ሕክምና ማዕከልም በክልሉ ጤና ቢሮ አሥተባባሪነት በአልማ እና በዩኒሴፍ መገንባቱን ገልጸዋል።

የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አሥፈፃሚ መላኩ ፈንታ
የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት በሚል እንቅስቃሴ አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች የልማት መስኮች ሢሠራ መቆየቱን ነው የተናገሩት።

የአልማ አቅም ሕዝቡ መኾኑን የገለጹት አቶ መላኩ እንደ ዩኒሴፍ አይነት አጋር አካላት ጋር በትብብር በመሥራት ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደፊትም እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የእናቶች እና ሕጻናት ሕክምና ማዕከል በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ እና የነበረውን ችግር የሚያቃልል መኾኑን ጠቅሰዋል።

ዋና ሥራ አሥፈፃሚው “ወደፊትም መሰል የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ሕዝቡ አጋዥ በመኾን ከጎናችን እንዲቆም” ሲሉ አሳስበዋል።

ከዚህ በፊት ለእናቶች አገልግሎት የሚሰጥበት ሕንጻ ጠባብ እና ደረጃውን ያልጠበቀ እንደነበር አገልግሎት እያገኙ ያሉ እናቶች ገልጸዋል።

አሁን ላይ አገልግሎት መስጠት የጀመረው እና የተመረቀው ማዕከል እነዚህን ችግሮች የፈታ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፡-መሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል የ2018 በጀት ዓመት ጥቅል በጀት 225 ቢሊዮን 453 ሚሊዮን ብር ኾኖ ፀደቀ።
Next articleየምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።