የኢትዮጵያን የቆዳ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በትብብር እና በቅንጅት መሥራት ይገባል።

8

አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው የመጀመሪያው ዘላቂ የቆዳ ምርት እና ፈጠራ ኮንፈረንስ ተካሄደ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ እና በርካታ ኢንቨስትመንቶች ከሚንቀሳቀሱባቸው ዘርፎች መካከል የቆዳ ኢንዱስትሪው ተጠቃሽ ነው።
ዘርፉ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከ800 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ የዘርፉ ማነቆ የኾኑባት የቆዳ ግብዓት እና የማምረት ችግሮች ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳታገኝ አድርጓት ቆይቷል።

ይህን ችግር መፍታት ዓላማው ያደረገ የመጀመሪያው ዘላቂ የቆዳ ምርት እና ፈጠራ ኮንፈረንስ መዘጋጀቱን የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክትር ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋየ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዘርፉን ለማዘመን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የሰው ኃይል እያሠለጠነ ወደ ገበያ እያስገባ ነው።

ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ የዩኒቨርሲቲ እና የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

በኮንፈረንሱ የተገኙት የአፍሪካ ቆዳ እና የቆዳ ምርቶች ኢንስቲትዩት ምክትል ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ገብረ መድኅን የዘርፉን ችግር በመፍታት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የምርምር፣ የአምራች እና የትምህርት ተቋማት በትብብር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስትር የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጄኔራል ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ.ር) በኮንፈረንሱ የዘርፉን ችግር መፍታት የሚያስችሉ የፖሊሲ የመመርመሪያ እና ሌሎች የማሻሻያ ሃሳቦች ግብዓቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

የዘርፉ ማነቆ የኾኑትን የግብዓት፣ የምርት ሂደት እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላችንን እንወጣለን” ወጣቶች
Next articleየአማራ ክልል የ2018 በጀት ዓመት ጥቅል በጀት 225 ቢሊዮን 453 ሚሊዮን ብር ኾኖ ፀደቀ።