
ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር “ሰላማችንን እንጠብቃለን፤ ልማታችንን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልዕክት በከተማዋ ከሚገኙ ተመራቂ ወጣቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩ ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ እና ሌሎች የልማት ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ታልሞ የተዘጋጀ ስለመኾኑ ተገልጿል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ተስፋዬ አዕምሮ ወጣቶችን በጎ ፈቃድ ሥራዎች በማሳተፍ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።
በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስ እና በመጠገን በከተማ ጽዳት እና ውበት ሥራዎች እና መሰል ተግባራት ላይ ወጣቶች ሰፊ ርብርብ እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
እስካኹንም 56 አዳዲስ ቤቶች በጎ ፈቃደኛኞችን በማስተባበር መገንባት ስለመቻሉ አብራርተዋል።
ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ሥራዎች በክረምት ብቻ ሳይወሰኑ በንቃት እንዲሳተፉም መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አበባው ግዛቸው የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የሰላም ባለቤት እንዲኾኑ ለማስቻል ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውንም አብራርተዋል።
በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የልማት ዘርፎች ላይ ወጣቶች ከፍተኛ ሚናቸውን እየተወጡ እንደኾንም ጠቁመዋል።
ኀላፊው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ኹኔታ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻሉ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሁለንተናዊ የወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ ግብ ተጥሎ እየተሠራበት መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ብዥታዎችን የማጥራት እና ወጣቶች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
ወጣቶች አልባሌ ቦታ ከመዋል ይልቅ ጊዜያቸውን በክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎች በመሳተፍ ሊያሳልፉ ይገባል ያሉት ደግሞ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።
ለሰላም ዕጦቱ ሥራ አጥነት አንዱ ገፊ መኾኑን ያነሱት ወጣቶች በርካቶች ያለሥራ ተቀምጠዋል ብለዋል። በመኾኑ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥም ወጣቶቹ ጠይቀዋል።
ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን