ደኖችን ስለመጠበቅ ሕጉ ምን ይላል?

22

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የክልል አቃቢ ሕግ ዘነበ አበጋዝ ከደን ልማት የሚገኘውን ከፍተኛ ሃብት ከጥፋት ለመጠበቅ የደን ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/2010 ጸድቆ በሥራ ላይ መዋሉን አንስተዋል።

በደን ሃብት ላይ የተከለከሉ ድርጊቶችን መፈጸም በወንጀል እንደሚያስቀጣም አንስተዋል።

የደን ባለቤትነት ዓይነቶች በአራት ተለይተው በአዋጁ ተጠቅሰዋል፤ እነሱም የግል ደን፣ የማኅበረሰብ ደን፣
የማኅበራት ደን እና የመንግሥት ደን ናቸው። በደን ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/2010 በአንቀጽ 25 ከንዑስ አንቀጽ (1) እሰከ (4) በደን ሃብት አጠቃቀም ላይ የተከለከሉ ድርጊቶች በግልጽ ተቀምጠዋል።

በመጀመሪያው አንቀጽ ሥር እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው በመጥፋት ላይ የሚገኙ በተፈጥሮ የበቀሉ ሀገር በቀል ዛፎችን ከመንግሥት ደን ውስጥ
እንዲኹም በተፈጥሮ በቅለው የሚገኙና በማኅበረሰብ ይዞታነት ሥር ካሉ ደኖች መቁረጥ አይችልም።

ማንም ሰው ሚመለከተው አካል የጽሁፍ ፈቃድ ካልተሰጠው ወይም በራሱ ይዞታ ላይ ካልሆነ በስተቀር ከማንኛውም ደን ውስጥ ዛፍ መቁረጥ፣ በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት መስፈር፣ የቤት እንስሳትን ለግጦሽ ማሰማራት፣ አደን ማካሄድ፣ የእንጨት መሰንጠቂያ መጋዞችና ሌሎች ለደን ጭፍጨፋ የሚረዱ መሣሪያዎች ይዞ መገኘት፣ ቀፎ መስቀል፣ ማር መቁረጥ ወይም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን መፈጸም እንደማይችልም በአዋጁ ተቀምጧል፡፡

የሕግ ባለሙያው ዘነበ አበጋዝ ከዚሁ ጋር አያይዘዉ ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ ማንኛውም በደን የተሸፈነ ወይም የደን መሬት ለልማት እንዲሰጥ ሲወሰን የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ቀርቦ በሚመለከተው አካል ይሁንታ ማግኝት ይኖርበታል።

በደን ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/2010 የተከለከሉ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች የሚጠብቃቸው ተጠያቂነት በአንቀጽ 26 ከተራ ቁጥር (1) እሰከ (8) ተዘርዝሯል። ከመንግሥት፤ ከማኅበረሰብ እና ከግል ደኖችና የደን መሬቶች ዛፎችን ከባለ ይዞታው ፈቃድ ውጭ የቆረጠ ወይም የደን ውጤቶችን የወሰደ፣ ለዚህ ተግባር የተባበረ ወይም በማንኛውም ሕገ ወጥ መንገድ የደን ውጤቶችን ይዞ የተገኘ ወይም የተጠቀመ ሰው የደን ውጤቱ መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከ10 እስከ 20 ሺህ ብር ገንዘብ ይቀጣል፡፡

የደን የወሰን ምልክቶችን ያጠፋ፣ ያበላሸ ወይም ያዛባ ማንኛውም ሰው ከአንድ ዓመት በማያንስ እና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከ10 እስከ 30 ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ ይቀጣል።

ሆን ብሎ እሳት በመለኮስ ወይም በማናቸውም ሌላ ኹኔታ በደን ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከ 10 ዓመት በማያንስና ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል። ጉዳቱ የደረሰው በቸልተኝነት ከሆነ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር እስከ 10 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ሲሉ አብራርተዋል አቃቢ ሕጉ፡፡

ደን እና የደን መሬት ተብሎ በተከለለ ስፍራ የሰፈረ ወይም የእርሻ ቦታ ያስፋፋ ወይም ማንኛውንም ግንባታ ያካሄደ ማንኛውም ሰው ከሁለት ዓመት በማያንስና ከአራት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከ10 እስከ 40 ሺህ
ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ያልተፈቀደ የደን ውጤት ያጓጓዘ ማንኛውም ሰው ከስድስት ወር በማያንስና ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከብር 5 ሺህ 10 ሺህ ይቀጣል፡፡

ማንኛውም የደን ባለቤት በደን ውስጥ ተባይ፣ ተስፋፊነት ያላቸው አረሞችና በሽታ መከሰቱን እያወቀ አግባብ ላለው አካል በአፋጣኝ ያላሳወቀ እንደሆነ ከስድስት ወር በማያንስና ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና
ከአንድ ሺህ እስከ አምስት ሺህ በሚደርስ ገንዘብ ይቀጣል፡፡

ማንኛውም የደን ባለቤት በደን ውስጥ ያልተፈቀዱ ዕፅዋትን፣ እንስሳትን ወይም ደቂቅ ነፍሳትን ያስገባ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማያንስና ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከብር 10 ሺህ እስከ 30 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ዝርያቸው በመጥፋት የሚገኙ የዛፍ አይነቶችን በሕገ ወጥ መንገድ ከመንግሥት፣ ከማኅበራት፣ ከማኅበረሰብ እና ከግል ይዞታ ላይ የቆረጠ፣ ያጓጓዘ፣ ያከማቸ እና ለሽያጭ ያቀረበ ሰው ከአምስት ዓመት በማያንስና ከስምንት ዓመት
በማይበልጥ ጽኑ እስራት፤ 15 ሺህ ብር እስከ 20 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል ብለዋል ሕጉን ጠቅሰው።

አቶ ዘነበ በደን ላይ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን መተው እንደሚያስፈልግም መክረዋል። ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግም የባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አማረ ካሳ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምክር ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት ለመንግሥት ሥራዎች ማስፈፀሚያ የታወጀ ተጨማሪ በጀት አዋጅን አጸደቀ።
Next article“ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላችንን እንወጣለን” ወጣቶች