
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤ አራተኛ ቀን ውሎውን እያካሄደ ነው።
ምክር ቤቱ በአራተኛ ቀን ውሎው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ የአሚኮን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም የላቀ ይዘት በማቅረብ የአድማጭ ተመልካችን እና የአንባቢያንን እርካታ ማሳደግ፤ የበቃ የሰው ኃይል በማቅረብ የላቀ የመፈጸም እና የማስፈጸም እቅምን ማሳደግ፣ የዘመነ ቴክኖሎጂ በማቅረብ እና በመጠቀም የሚዲያውን የዘገባ ጥራት እና ተደራሽነትን ማሳደግ፣ ዘላቂነት ያለው ውጤታማ ሃብት በማመንጨት ቅልጥፍና እና ጥራት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት የሚሉ የትኩረት መስኮችን እና ግቦችን በማስቀመጥ የበጀት ዓመቱን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አማራ ሚደያ ኮርፖሬሽን በ30 ዓመታት የሚዲያ ጉዞው አራት የጋዜጣ ውጤቶች፣ ሰባት ራዲዮ፣ ሁለት የቴሌቪዥን ማሠራጫዎች፣ ሁሉንም የሚዲያ አማራጮች በአንድ ማዕቀፍ ማቅረብ የሚችል ጠንካራ የዲጂታል ማዲያ ባለቤት መኾኑን ገልጸዋል።
ዘገባዎቹ አካታችነትን እና ብዝኀነትን በሚያሳድግ መልኩ የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ተደራሽ በመኾን በርዕይ ደረጃ ያስቀመጠውን ግብ በማሳካት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ላለፉት ዓመታት ሲያቀርብ የነበረውን አገልግሎት በላቀ ደረጃ አማራጭን በሚያሰፉ መንገዶች ለመስጠት የሚያስችለውን የሪፎርም ሥራ በውጤታማነት በመተግበር በ2016 በጀት ዓመት “አሚኮ ወደ አዲስ ሞዕራፍ” በማለት ዘርፈ ብዙ የአሠራር እና የይዘት ማሻሻያ ሲያከናውን መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ የተሠሩ የማሻሻያ ሥራዎችን ወደ ውጤት ለመቀየር የሚያስችል በጀት ዓመት አንዲኾን በሁሉም የአሚኮ ቤተሰቦች መግባባት በመፍጠር በጀት ዓመቱን “የመፈጸም በጀት ዓመት” በሚል መሪ መልዕክት ሁሉን አቀፍ የትግበራ ሥራዎችን በጥራት እና በቅልጥፍና ለመፈጸም ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።
የአሚኮ ሠራተኞችን አቅም የማሳደግ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል።
የእሚኮ ሠራተኞች የሀገሪቱን እና የክልሉን ትክክለኛ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመረዳት የአመለካከት አንድነት በማምጣት በሁሉም ደረጃ የሚሰጡ ተልዕኮዎችን በጥራት እና በቅልጥፍና የመፈጸም እቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
የኢቲዮ ኮደርሰ ሥልጠና ኢኒሼቲቭ ከሚዲያ አንጻር ቁልፍ ተግባር መኾኑን በመረዳት የአሚኮ ሠራተኞች ሥልጣናውን እንዲወስዱ መደረጉን ገልጸዋል። ይህም በኢትዮጵያ የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ቀዳሚ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተጠቃሚ ለኾነው አሚኮ አበርክቶው የላቀ ነው ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን ፊት ለፊት እየተጋፈጠ በሌላ በኩል ለነገ ተቋም ግንባታ የሚኾን የሪፎርም ሥራዎችን በመተግበር ልህቀትን ሊያረጋግጥ የሚችል የምዘና ሥርዓት ትግበራ ውስጥ እንደገባ አንስተዋል።
በዚህም የኮርፖሬት ሥራ ባሕልን መሠረት ያደረገ ከዚህ በፊት ሲሰጥ ከነበረው የስድሰት ወር ምዘና ሥርዓት በመውጣት በየሦሥት ወሩ መመዘን የሚያስችል ትግበራ ውስጥ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የሚዲያውን የቀጣይ ዓመታት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ትልቅ አበርክቶ የሚኖረው ተቋም ለመገንባት ነገን የተለመ የአምስት ዓመታ ስትራቴጂክ ዕቅድ መታቀዱን ገልጸዋል። አሚኮ ዘመኑን የዋጁ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች እየተጠቀመ መኾኑንም አመላክተዋል።
ለሚዲያ መሠረተ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ዘመናዊ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ስቱዲዮ ገንብቶ ሥራ ማስጀመሩንም አንስተዋል። በአዲስ አበባ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለመገንባት ቦታ ተረክቦ በ2018 በጀት ዓመት ወደ ግንባታ ይገባል ብለዋል። በደሴ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የሚዲያ ኮምፕሌክስም 49 በመቶ መድረሱንም አንስተዋል።
የሰቆጣ ኤፍኤም ግንባታን በልዩ ስምሪት አጠናቅቆ ርክክብ መደረጉንም ገልጸዋል።
የክልሉን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነቶች ጠንካራ ትስስር ካለው የሱዳን ሕዝብ ጋር ለማስተሳሰር የገንዳ ውኃ ኤፍኤም ግንባታ ለማከናወን የቦታ ርክክብ በማድረግ የዲዛይን ሥራውን በማጠናቀቅ በ2018 በጀት ዓመት ወደ ተሟላ ግንባታ ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል።
አሚኮ በበጀት ዓመቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ የተደረጉ
የሰላም ጥሪዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘገባዎችን ትኩረት ሰጥቶ ሽፋን መስጠቱን ተናግረዋል።
ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ የሚያግዙ ዘገባዎችን በቀረጻ እና በቀጥታ ስርጭት ማኅበረሰቡን በሚያሳትፍ መንገድ ሽፋን ለመስጠት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።
የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ቀበሌ ድረስ በመውረድ ስለ ሰላም እና ልማት ኅብረተሰቡን ያወያዩባቸውን መድረኮች መሠረት ያደረጉ ዘገባዎች በትኩረት ተሠርተዋል ነው ያሉት።
የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የሚረዱ ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ ቀናትን መሠረት ያደረጉ ልዩ ዝግጅቶችን በቀጥታ ስርጭት እና በቀረጻ ሽፋን በመሰጠት ገጽታ ለመገንባት የተሠራው ሥራ ውጤታማ ነበር ነው ያሉት።
አሚኮ በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራዎች፣ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሚያስችሉ ሥራዎችን እና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።
በሀገራዊ ጉዳዮች አብሮነትን ለማጠናከር የተለያዩ ዘገባዎችን በመሥራት ለገዥ ትርክት ግንባታ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ተደርጓል ነው ያሉት።
ነጻ የኾነ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ማኅበራዊ ኀላፊነቱን መወጣቱንም ገልጸዋል። አሚኮ ለመላው ኢትዮጵያውያን የዘገባ ሽፋን በመስጠት ለሀገር አንድነት ተጨማሪ አቅም ኾኗል ነው ያሉት።
በ2017 በጀት ዓመት ለክልሉ ገጽታ ግንባታ እና ሁሉ አቀፍ ሁኔታ ማስረዳት አቅም ኾነው ማገልገል የቻሉ ከ30 በላይ የቀጥታ ስርጭት ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በመላ ሀገሪቱ ወንድማማችነት መሠረት ያደረጉ ዘገባዎችን መሥራቱን ገልጸዋል። አሚኮ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱ እያደገ መምጣቱንም አንስተዋል። እንደ ሀገር ባበረከተው አስተዋጽኦ በፌዴራል ደረጃ የአንደኛ ደረጃ ተሸላሚ መኾኑንም አንስተዋል።
አሚኮ የበለጠ ውጤታማ እንዲኾን ለማድረግ የክልሉ መንግሥት የሚያደርገውን የተጠናከረ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የአሚኮ ሠራተኞች የገጠማቸውን ችግር በመቋቋም የሠሩት ሥራ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል። በፈተና ውስጥ ኾኖ ይዘትን ማሻሻል፣ ፕሮጄክት መምራት እና ሕዝብን ማገልገል እንደሚቻል አሳይታችኋልና እናመሠግናለን ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የክልሉን አሻጋሪ ዕቅዶችን መሠረት ያደረጉ፣ የአሚኮን ቀጣይ ጉዞዎች በመሠረታዊነት ማሳደግ የሚችል የስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራ ውስጥ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን