
ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የሦስተኛ ቀን ውሎ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አድምጧል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት ፍርድ ቤቶች ለሕግ የበላይነት፣ ለመልካም አሥተዳደር መረጋገጥ እና ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር ዋነኛ እና የመጨረሻ አማራጭ ተቋማት ናቸው፡፡
በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በክልሉ የፍትሕ አሥተዳደር ሥርዓት በተለይ ደግሞ በዳኝነት ሥርዓቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ፍርድ ቤቶች አሠራርን ለማዘመን እና ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፍትሕ ቢሮዎችን የማዘመን ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
የፍርድ ቤት ተገልጋዮች ባሉበት አካባቢ ኾነው እንዲከራከሩ፣ ፋይል ማስከፈት እንዲሁም አቤቱታ ማቅረብ የሚችሉበት የዲጂታላይዜሽን ሥራ በከፍተኛ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠናቅቆ ለሥራ ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ታራሚያዎች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሔድ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ኾነው እንዲከራከሩ በባሕር ዳር ማረሚያ ቤት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ አሠራር ተግባራዊ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡
በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶችም ምቹ የሥራ ቦታ ለመፍጠር እና የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት እውን ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ፦
👉 4 ሺህ 481 ተከሳሾች ነጻ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም በ1 ሺህ 757 መዛግብት ውስጥ የሚገኙ 2 ሺህ 33 ተከሳሾች ውሳኔ አግኝተዋል፡፡ በ1 ሺህ 413 መዝገቦች ውስጥ የሚገኙ 2 ሺህ 448 ተከሳሾች ጉዳይ ደግሞ በቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
👉 33 ሺህ 199 አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እና ህጻናት በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ቅድሚያ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡
ሌላኛው በበጀት ዓመቱ ትኩረት የተሠጠው ደግሞ የፍርድ ቤት አስማሚነት ሥርዓት ማጠናከር ነው፡፡
👉 በዚህም በበጀት ዓመቱ ለአስማሚዎች ከቀረቡ 3 ሺህ 230 መዛግብት ውስጥ 2 ሺህ 72 መዛግብት በሥምምነት ተቋጭተዋል፡፡
👉 979 ባለጉዳዮች ባለመስማማታቸው ወደ መደበኛው ችሎት ለክርክር እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
👉 179 መዛግብት ደግሞ በመታየት ላይ ይገኛሉ፡፡
👉 በበጀት ዓመቱ በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች 435 ሺህ 325 መዝገቦች የቀረቡ ሲኾን 90 ነጥብ 37 በመቶ የሚኾ መዛግብት እልባት አግኝተዋል፡፡
አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ4 ነጥብ 07 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡
👉 የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተዘዋዋሪ ችሎት፣ አመራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን እና የሸሪአ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ በየደረጃው በሚገኙ የሸሪአ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡት 11 ሺህ 841 ጉዳዮች ውስጥ ከ93 በመቶ በላይ የሚኾኑ ጉዳዮች እልባት ማግኘታቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በክልሉ አለመግባባቶችን በባሕል ፍርድ ቤቶች ለመፍታት የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ መጽደቁን ገልጸዋል፡፡ የአዋጁ ትግበራ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ የመመሪያዎች ዝግጅትም ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
ፍርድ ቤቱ የጀመረውን የለውጥ ሥራ ማጠናከር፣ የባለሙያዎች አቅም እና ሥነ ምግባር ግንባታ፣ የፍርድ ጥራት እና ቅልጥፍናን ማሳደግ፣ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክን ማጠናከር፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች በተለይም የባሕል ፍርድ ቤቶችን እውቅና መስጠት እና የዳኞችን ነጻነት እና ተጠያቂነት በተሟላ ሁኔታ ማረጋገጥ በ2018 በጀት ዓመት ትኩረት የተሠጣቸው ተግባራት ናቸው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!