በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ 50 ሺህ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

345

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባለፈው ዓመት በሕዝብ ተሳትፎ ከከተተከለው ችግኝ ውስጥም 68 በመቶ መጽደቁን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አስታውቋል፡፡

የአፍሪካ ጣሪያ፣ የዓለም ብቸኛው ዝርያ ዋሊያ መኖሪያ፣ የተንሰላሰሉ ተራሮች መንደር እና የተባዘተ ዳመና የማይለየው ልዩ ቦታ ነው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፡፡ ፓርኩ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ሕዝቦች ሀብት ቢሆንም በተደጋጋሚ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ፈትነውታል፡፡ ባለፈው ዓመት በፓርኩ የተከሰተው የእሳት አደጋም ለበርካቶች የማይረሳ ክስተት ነበር፡፡ በዘርፉ ባለሙያዎች ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ቀደመ ሁኔታው ለመመለስ እስከ 10 ዓመታት ይወስድበታል ቢባልም ቦታው ከነበረው ውስጣዊ ፀጋ አንጻር በአጭር ጊዜ ማገገሙን ከዚህ በፊት ዘግበን እንደነበር ይታወሳል፡፡

በባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከክልሉ የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ፓርኩ አቅንተው ችግኞችን ተክለዋል፡፡ ከ38 ሺህ 400 በላይ ስድስት ዓይነት ሀገር በቀል ችግኞች ተተክለው እንደነበር የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አበባው አዛናው ተናግረዋል፤ በተደረገ ቆጠራ ከ68 በመቶ በላይም መጽዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡

መጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ችግኞችን የመንከባከብ መርሀ ግብር እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ በተፈጠረው ወቅታዊ የጤና ስጋት ምክንያት እንዳልተካሄደም አስታውቀዋል፡፡ “ምንም እንኳን በተፈጠረው የጤና ስጋት ምክንያት ቢሆንም በችግኝ ተከላ የታየው ሕዝባዊ ተሳትፎ ችግኞቹን በመከታተል በኩል ግን ውስንነት ነበረበት” ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡
በያዝነው የክረምት ወቅት በፓርኩ ከ50 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መጀመሩንም አቶ አበባው አስታውቀዋል፡፡ ችግኞቹ በደባርቅ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት እና በፓርኩ ችግኝ ጣቢያዎች እንደተዘጋጁም ገልፀዋል፡፡ የደባርቅ እና የጎንደር ከተሞች የወጣት ማኅበራትም በፓርኩ ችግኝ ለመትከል ጥያቄ ማቅረባቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ተጋላጭነትን በሚከላከል መልኩ ከሐምሌ መጀመሪያ አንስቶ ለ15 ቀናት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደሚኖር አቶ አበባው አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየግብዓት እጥረት እንዳጋጠማቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
Next articleዛሬ የተጀመረው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቀጣይ ሥራዎች ግንዛቤ መፍጠሪያ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡