
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር እንደ ክልል በባሕር ዳር ከተማ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስጀምሯል፡፡
በዝግጅቱ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች እና የከተማዋ ነዋሪ ሴቶች እና ሕጻናት ተገኝተዋል፡፡
ችግኝ የተተከለው በሽምብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲኾን ተሳታፊዎች ከችግኝ ተከላ በኋላ ደም ለግሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የዛሬው መርሐ ግብር ሴቶች እና ሕጻናት “በመትከል ማንሠራራትን” በጋራ የሚከውኑበት መርሐ ግብር መኾኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ክልል ሴቶች እና ሕጻናትን በማሳተፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ በማሳደግ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሚደረግ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ችግኝ ተከላው ትምህርት ቤት ላይ የኾነው በምክንያት ነው ያሉት ኀላፊዋ ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ላይ የምገባ ሥርዓት እየተካሄደ በመኾኑ የሚተከሉ ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ችግኝ መትከል ለሕጻናት እና ለሴቶች በአካባቢ የሚመገቡትን እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል፡፡
ኀላፊዋ ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን ደም ልገሳው ላይ ደም መለገስ የሚችሉ ሁሉም እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የክረምት ወቅት በርካታ የበጎ ፈቃድ ሥራ የሚሠራበት እንደኾነ አንስተዋል፡፡
“ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ ሌሎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በመሥራት ለተቸገሩ ወገኖች ለወገን ደራሽ መኾናችንን የምናሳይበት ሊኾን ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ችግኝ ሲተክሉ አሚኮ ያገኛቸው ሕጻን አንጓች ደቤ እና ሕጻን መሠረት ጌታቸው ችግኝ በመትከላቸው ደስተኛ መኾናቸውን እና ወደፊት እንደሚንከባከቡት ተናግረዋል፡፡
የተከሏቸው ችግኞች ሲያድጉ በትምህርት ቤት ጥላ እንደሚኾናቸው እና ለምግብነትም እንደሚጠቀሙበት ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን