
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት ግርማይ ታዴ በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪ ሲኾን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በንብ ማነብ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ ይገኛል፡፡
ወጣት ግርማይ ከዚህ በፊት ከረጅ ድርጅቶች ባገኘው የዘመናዊ ቀፎ የተሻለ ምርት ማግኘቱን ነው የገለጸው፡፡
ምርቱን ንጹህ ከማድረግና ለረጅም ጊዜ ለማቆየት በሚቆረጥበት እና በሚቀመጥበት ጊዜ ጥንቃቄ እንደሚደረግ አንስቷል፡፡ ማር በሚቆረጥበት ጊዜ ከኩበት ጭስ ይልቅ የወይራ ጭስ በመጠቀም በምርቱ ላይ ተጽዕኖ እንዳይኖር እንደሚያደርግ ነው የገለጸው፡፡
ለንቦች ተስማሚ የኾኑ ዕጽዋትን፣ ቅመማ ቅመሞችን በመትከል እና በሌሎች ተባዮች ንቦች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በባሕላዊ መንገድ የመንከባከብ ሥራ እንደሚሠሩም ተናግሯል፡፡
እነዚህን ሥራዎች በመሥራታቸውም በ2017 በጀት ዓመት ሦስት ጊዜ በመቁረጥ ከ15 ዘመናዊ እና ከ10 ባሕላዊ የንብ ቀፎዎች 220ኪሎ ግራም የማር ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የማር ምርት ሥራ በሰፊውና ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራበት አዋጭና ገበያ ላይ ተፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲሳይ አያሌው ዞኑ ከፍተኛ የንብ ሃብት ያለበት ሲኾን ከ100ሺህ በላይ የንብ መንጋ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ በዘመናዊ ቀፎ የሚጠቀመው ከ10 በመቶ አይበልጥም ነው ያሉት፡፡ ሌላው ገና ከባሕላዊ ቀፎ ያልተላቀቀ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ 1ሺህ 235ቶን የማር ምርት ተመርቷል፤ ይህም አብዛኛው ከባሕላዊ ቀፎ የተገኘ ምርት መኾኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ በጀት ዓመት የማር ምርት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ችግሮችንም ጠቅሰዋል፡፡ ከሰብል ልማት ጋር ተያይዞ ሕገ-ወጥ የጸረ-ተባይ ኬሚካል ርጭት ለንቦች ርባታ አስቸጋሪ እና ንቦችን በከፍተኛ ኹኔታ እየጎዳ ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ይህም ርጭቱ የሚካሄደው በአበባ ወቅት በመኾኑ ንቦች ለቀሰም በሚወጡበት ጊዜ ጉዳት የሚያደርስ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
ሌላው ችግር የግብዓት ችግር ሲኾን የተሻሻለ ቀፎ አቅርቦት ችግር አለ ብለዋል፡፡ ወጣቶችን በተፋሰስ በማር ምርት ላይ በማሰማራት ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ቢኖርም ቀፎ ለማቅረብ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመኾኑ እየተሠራበት እንዳልኾነ ነው ኀላፊው የተናገሩት፡፡
ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ እስከ 35 ኪሎ ግራም የሚመረት በመኾኑ በዘመናዊ ቀፎ ቢሠራ አዋጭ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ከግብርና ጋር በጋራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ማር ማምረት በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተለመደ እና በአብዛኛው አርሶ አደር ቤት የሚሠራ ሥራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የማር ምርት ከማምረት ገበያ እስከ ሚቀርብበት ንጽህናውን እንዲጠብቅ ለማድረግ ማር ሲቆረጥ የኩበት ጭስ እንዳይጠቀሙ፣ ኬሚካል በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና የተፈቀዱ የማር ማስቀመጫ እቃዎችን እንዲጠቀሙ የማስገንዘብ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም መሻሻል አለ ከባሕላዊ ማስቀመጫ ወደ ፕላስቲክ እየተቀየረ ነው፤ ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ ባለመኾኑ ወደፊት በሰፊው መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡
እንደ ብሔረሰብ አሥተዳደር ያለው ችግር የግብዓት እና የቴክኖሎጅ አቅርቦት በመኾኑ የተሻሻለ ቴክኖሎጅ የሚያቀርቡ ፕሮጀክቶች ባለመኖራቸው ዞኑ ያለውን ጸጋ አልተጠቀመበትም ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብ እና ሃር ልማት ባለሙያ ሙሃመድ ጌታሁን የማር ምርቱን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ክልል 80 በመቶ የሚኾነው የማር ምርት የሚገኘው ከባሕላዊ ቀፎ በመኾኑ ወደ ዘመናዊ ቀፎ የማዛወር ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከአንድ የባሕላዊ ቀፎ እስከ 10 ኪሎ ግራም እና ከዘመናዊ ቀፎ ደግሞ እስከ 35 ኪሎ ግራም የማር ምርት የሚገኝ በመኾኑ ሽግግሩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመትም 45ሺህ 264 የሽግግር ቀፎዎችን መሥራት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥራት ያለው ምርት ወደ ገበያ እንዲቀርብ በባለሙያዎች ድጋፍ እና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
አቀማመጡም በባሕላዊ በእንስራ እና በጆንያ ማስቀመጥ እየቀረ ለምግብ ማስቀመጫ በሚመረቱ የፕላስቲክ ምርቶች የማስቀመጥ ባሕል እየዳበረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪ የማር ምርትን በማጣራት እና በማሸግ የአካባቢውን መለያ በመጠቀም ለማዕከላዊ ገበያም እየተላከ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ምርታማነቱን ለመጨመር ዘመናዊ ቀፎን መጠቀም ቁልፍ ጉዳይ ቢኾንም አርሶ አደሮች ከመንግሥት መጠበቅ እንጅ ገዝቶ መጠቀምን ባሕል አላደረገውም ብለዋል፡፡ ይህንንም ለማሻሻል የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች በሰፊው እየተሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ በ2017 በጀት ዓመት 29 ሺህ 698 ቶን የማር ምርት መገኘቱንም ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን