
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የአራተኛ ቀን ውሎውን ጀምሯል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም በአጭር ጊዜ የሕንጻ ዕድሳት፣ የአዲስ ሕንጻ ግንባታ እና የዲጂታላይዜሽን ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙት ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጭ ቆጣቢ፣ ተገማች፣ ጥራት እና ወጥነት ያለው ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት ፍትሕን ለማስፈን ነው ብለዋል። በፍርድ ቤቱ የዜጎችን በነጻ ችሎት የመዳኘት መብት ለማረጋገጥ መሠራቱንም ተናግረዋል። ዲጂታላይዜሽንን ተደራሽ ማድረግ የለውጥ ማጠንጠኛ ኾኖ እንደተሠራበትም ገልጸዋል።
የመንግሥት ተቋማት እና የልማት ድርጅቶች ፍርድን በመፈጸም እና በማስፈጸም ረገድ ሚናቸው ጉልህ ነው ብለዋል። የተሰጠ ፍርድ በበላይ ፍርድ ቤት አስካልተሻሻለ ወይም እስካልተሻረ ድረስ መፈጸም እንዳለበትም ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ ከሚሠራው ሠፊ ሥራ አንጻር ከፍተኛ በጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ካለው ድርሻ አንጻር ከፍ ያለ በጀት እንዲመደብለትም ጠይቀዋል።
በወረዳ ፍርድ ቤቶች የማስቻያ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። በተለይም በወረዳዎች እና በከተማ አሥተዳደሮች የማስቻያ ቦታዎችን ለማዘመን ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በታማኝነት እና በቅንነት ሕዝብን የሚያገለግሉ ዳኞች መኖራቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ የሚለቁ ዳኞች መኖራቸውንም አንስተዋል። የባሕል ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ መሠራቱንም ገልጸዋል።
ብቁ እና ተወዳዳሪ የኾኑ ዳኞችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል። በዲጂታላይዜሽን የታገዘ የዳኝነት ሥርዓትን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ለማውረድ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ዜጎች ባሉበት ኾነው ፍርድ እንዲያገኙ ዲጂታላይዜሽንን ማስፋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኪሚቴ አባል አስናቀች ኃይሌ የቋሚ ኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።
እንደ ሀገር አርዓያ የሚኾን ፍርድ ቤት ለመገንባት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል። የለውጥ ሥራዎችን መሥራት፣ ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠር የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት ለማረጋገጥ የተሠራው ሥራ በጥንካሬ የሚነሳ ነው ብለዋል።
ፍርድ ቤቶችን ለዘመናት ከቆዩባቸው ኋላቀር አሠራሮች በማውጣት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ ለመሥራት የተደረገው ጥረት የሚበረታታ መኾኑን ተናግረዋል። በቴክኖሎጂ የተደገፉ የፍርድ ቤቱ ሥራዎች በጥንካሬ የሚነሱ ናቸውም ብለዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተጀመረውን ምቹ የሥራ ከባቢ ወደ ታች ማውረድ እንደሚገባም አንስተዋል። በግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን ፍርድ ቤቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። የዳኞችን ሙያዊ ሥነ ምግባር በማሳደግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የዳኝነት ሥርዓቱን ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ማስጠበቅ ይገባልም ነው ያሉት።
የምክር ቤቱ አባላትም ፍርድ ቤቱ እያከናወናቸው የሚገኙ የለውጥ ሥራዎች የሚበረታቱ መኾናቸውን ገልጸዋል። የዜጎችን በነጻ ችሎት የመዳኘት መብት ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ ጅምር ሥራዎች የሚደነቁ መኾናቸውን አንስተዋል።
የለውጥ እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ማውረድ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። የዜጎችን መብት ሊያስከብሩ የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዳኞች የለውጥ ሥራውን እንዲሸከሙ ሥልጠና በመስጠት ለሥራ እንዲነሳሱ መደረጉ የሚደነቅ ነው ብለዋል። ብቁ ተወዳዳሪ የኾኑ ዳኞችን ማፍራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የዳኝነት ሥርዓቱን በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ለመምራት የተደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት አባላቱ የዳኞችን ፍልሰት ማስቆም እንደሚገባም ገልጸዋል። ተገልጋዮች የሚያነሱትን ቅሬታ የሚመልስ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አብራርተዋል። ብዙ ተገልጋይ እና ብዙ ችግር ያለው ወረዳ ፍርድ ቤቶች ላይ መኾኑን አንስተዋል።
የለውጥ ሥራዎች ውጤታማ የሚኾኑት የታችኛውን መዋቅር ማስተካከል ሲቻል ነው ብለዋል። የፍትሕ ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚገባም አመላክተዋል። እየተገነቡ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
ምክር ቤቱ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትንም አጽድቋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን