
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መሪዎች እና ሙያተኞች በባሕር ዳር ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ሥራ አስጀምረዋል። መሪዎች እና ባለሙያዎች የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላም አካሂደዋል።
በመርሐ ግብሩ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በመንግሥት እና በፓርቲ አደረጃጀት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሰው ተኮር የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አቶ ይርጋ ሲሳይ ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የበጋ እና የክረምት ተግባራትን አጣምረን እየሠራን ነው ብለዋል።
“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚለው መርሐ ግብር መሠረት የጽሕፈት ቤቱ መሪዎች እና ሠራተኞች ጥራት ያለው ቤት በአጭር ጊዜ አድሰው ለባለቤቶች እንደሚያስረክቡም ገልጸዋል። ይህንን አይነት ተግባር ሌሎችም ተቋማት እንደምሳሌ በመውሰድ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አቶ ይርጋ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉትን ነዋሪዎች ለመደገፍ በልዩ ንቅናቄ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
መሪዎች እና ባለሙያዎች በከተማው በተዘጋጀ የችግኝ መትከያ ቦታም ችግኝ ተክለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የጽሕፈት ቤቱ መሪዎች እና ሠራተኞች ላደረጉት በጎ ተግባር አመስግነዋል። ለሌሎች ተቋማትም ምሳሌ የሚኾን ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአቅመ ደካሞችን የቤት ችግር ለመቅረፍ ያደረጉት ድጋፍ ሕዝባዊ አመራርነትን ያረጋገጠ እንደኾነ ገልጸዋል።
ለከተማ አሥተዳደሩ ተጨማሪ አቅም እና ለኀብረተሰቡም መነሳሳትን የሚፈጥር መኾኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን