
ሁመራ፡ ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጠገዴ ወረዳ ስምንት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ በክልሉ በጀት ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የወረዳው አሥተዳደር ገልጿል።
የዞኑ ከፍተኛ ኀላፊዎች እና የአጎራባች ወረዳ አሥተዳዳሪዎች በተገኙበት የተመረቀው መንገድ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት የወረዳው መንገድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ አሳምነው ተናግረዋል።
በቀጣዩ በጀት ዓመት ሌሎች አዳዲስ መንገዶችን እና ድልድዮችን በመሥራት የኅብረተሰቡን የመንገድ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ነው ኀላፊው የጠቆሙት።
ወረዳው ለበርካታ ዓመታት ከመሠረተ ልማት ተገልሎ የቆዬ እንደነበር ያነሱት የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ አዛናው ከፍያለው ናቸው።
ከለውጡ በኋላ ከመንገድ መሥራት እና መጠገን ጀምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
የዞኑ መንገድ መምሪያ ኀላፊ ተመርጣ መብራቱ የዞኑ እና የወረዳው ሕዝብ እንኳን ልማቱን ማንነቱን ተነፍጎ የነበረ መኾኑን አስታውሰዋል።
በልማት ተጎድቶ የነበረ አካባቢ ነበር ያሉት ኀላፊዋ ከለውጡ ወዲህ በክልሉ መንግሥት ድጋፍ እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በርካታ መንገዶች ተገንብተው ለሕዝብ አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
ይሄ መንገድም ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
መንግሥት እና ሕዝብ በሀሳብ፣ በጉልበት እና በገንዘብ ከተደጋገፈ ልማትን ማስቀጠል ይቻላል ሲሉ የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ እና የዞኑ አሥተዳዳሪ ተወካይ ጌታቸው ሙሉጌታ ተናግረዋል።
በዞኑ እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶች የዚህ ማሳያ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ኅብረተሰቡ ለሰላም እና ለልማት እያደረገው ያለውን ንቁ ተሳትፎ በማጠናከር አካባቢውን ለማልማት እና የወሰን እና ማንነት ጥያቄውን በሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት መደገፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
የዞኑ ሕዝብ ሀገራዊ ለውጡ መምጣቱን ተከትሎ በርካታ ድሎችን ተጎናጽፏል ያሉት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ ናቸው።
በራስ ቋንቋ መናገር፣ ባሕል እና ወግን በነጻነት ማንጸባረቅ እና ማንነትን ማስከበር መቻሉን ገልጸዋል።
“እኛ ራስን የመኾን ትግል ላይ ነን” ያሉት አቶ ገብረእግዚአብሔር ለዚህም ብልጽግና ፓርቲ ምቹ ኹኔታዎችን መፍጠሩን አስረድተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማራዊ ማንነቱን ለማጽናት እየታገለ ልማቱንም በማፋጠን ላይ ነው ብለዋል።
ከማክሰኞ ገበያ- ዳራ ደቅአባ የተጠገነው መንገድ በፊት የኅብረተሰቡን እንቅስቃሴ ያስተጓጉል እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተጠገነው መንገድ ደስተኛ ነን ያሉት ነዋሪዎቹ መንገድን ጨምሮ በሌሎች መሠረተ ልማቶች እየተደረገ ያለው ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉን አድንቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን