“ጦርነት እና ግጭት በዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ግንባታ ላይ ትልቅ እንቅፋት ናቸው” አንቶኒዮ ጉተሬዝ

16

አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ሀገራት የምግብ ሥርዓታቸውን ለማጠናከር የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ እና የፖሊሲ ትግበራ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዋና ጸሐፊው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የምግብ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማ የሚኾነው ሁሉን አቀፍ፣ ፍትሐዊ እና የማይናወጥ ሲኾን መኾኑን አብራርተዋል።

ጦርነት እና ግጭት በዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ግንባታ ላይ ትልቅ እንቅፋት መኾናቸውን ጠቁመው በሱዳን የተከሰተው ሰፊ ረሃብም የዚህ ውጤት መኾኑን በምሳሌነት አንስተዋል።

ጉተሬዝ በ2030 ረሃብን ዜሮ ለማድረግ በ17ቱ ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ በሀገራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ የስንዴ ምርትን በማሳደግ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

ዋና ፀሐፊው የዚህ ሁሉ ጥረት ዋና ዓላማ ለሰው ልጅ የተሻለ ነገርን መፍጠር መኾኑን ጠቅሰዋል።

የተሻሻለ የምግብ ሥርዓት መገንባት ለሰው ልጅ ሁሉ መሠረታዊ መብት መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥም ዓለም ውጤት እንደምታገኝ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሀገራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋጥ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል።
Next articleበጠገዴ ወረዳ ብልሽት ገጥሞት የነበረ መንገድ ተጠግኖ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።