
አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ያዘጋጁትን እና በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘውን ሁለተኛውን የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ከፍተዋል።
በመክፈቻው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰው ልጅ እና የቡና መገኛ ወደኾነችው ኢትዮጵያ እንኳን በደኅና መጣችሁ ብለዋቸዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት አካታች እና ፍትሐዊ በኾነ መልኩ እንዲተገበር እየሠራች ነው ብለዋል።
የምግብ ሥርዓቱ አካታች በኾነ መልኩ ይሠራል ሲባል ግብርና ብቻ ሳይኾን የአካባቢ አየር ንብረት ጭምር በተስተካከለ መልኩ አንዲቀጥል ማድረግ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ቢኾንም ጠንካራ እና ራሱን የሚቋቋም የምግብ ሥርዓት መገንባቱንም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን ለመቻል ራሷ ላይ በመሥራት በከተማ እና በገጠር ሁሉም ራሱ እንዲያመርት እያደረገች ነው ብለዋል።
በበሀገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳ በመመራት የግብርና ለውጥ እና ፋይናንስን በማሳደግ ለዘርፉ ዕደገት በአግባቡ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
“ግባችን ግልጽ ነው፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተመጣጠነ እና በቂ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)። የፕሮጀክቶቹ ሁሉ ግብ እና መዳረሻም ይኸው መኾኑን አንስተዋል።
በምግብ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ በ7 አቅጣጫዎች የተተለሙ 700 የሚደርሱ ትግበራዎችን ማከናወን እንደተቻለም አስረድተዋል።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም የሌማት ቱሩፋት አንዱ ሲኾን ሁለገብ የኾነ የተመጣጠነ ምግብ ማኅበረሰቡ እንዲያገኝ የሚያደርግ ትግበራ እንደኾነም አብራርተዋል።
የሰቆጣ ስምምነት ሕጻናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሌላኛው ፕሮጀክት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አካታች የገጠር ልማት እና ፋይናንስ ሥርዓት አርሶአደሮች ከገበያ እና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በማገናኘት ምርትን የሚጨምር ትልቅ የኢትዮጵያ ርምጃ እንደኾነም ተናግረዋል።
የትምሀርት ቤት ምገባም ሀገርበቀል ትልቅ ትግበራ እንደኾነ ጠቁመዋል። ይህም ጤናቸው እና አዕምሮው የተስተካከለ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል ስለመኾኑ ነው ያስረዱት።
ቴክኖሎጂው በግብርናው ላይ ትልቅ ስፍራ እንዲይዝ እየተሠራ እንደኾነም አብራርተዋል። ይህ ደግሞ በቂ ምግብ በማምረት በምግብ ሥርዓት ለውጥ ውስጥ ትልቅ ስፍራን እንደሚይዝም ነው የጠቆሙት።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን