ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ፣ ሥልጣን እና ተግባራት መወሰኛ አዋጅን አጸደቀ።

89

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ የሦስተኛ ቀን ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

በሦስተኛ ቀን ጉባኤው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሻሻለው የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ፣ ሥልጣን እና ተግባራት መወሰኛ አዋጅን አጽድቋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሻሻለው የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ ሥልጣን እና ተግባራት መወሰኛ አዋጅን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

የተሻሻለው የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ እና ሥልጣንና ተግባራት መወሰኛ አዋጅን የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ በክልሉ ያሉትን የመልማት ፀጋዎች አውጥቶ ለመጠቀም፣ የድህነት እና የግጭት አዙሪቶች በማስቀረት የትውልዶች ጥያቄ የነበረውን ብልጽግና እውን ለማድረግ መንግሥታዊ ተቋማትን ፈትሾ እንደገና ማደራጀት ማስፈለጉን ገልጸዋል።

እንደ ክልል የተሸረሸሩ እሴቶችን፣ ወጎችን እና ባሕሎችን በመንገባት፣ ሰብራቶችን በመጠገን በሥነ ምግባር የታነጸ ሀገር ወዳድ ትውልድ የማፍራት ተልዕኮ የሚሸከም ውጤታማ ተቋማት ለመፍጠር ተቋማትን እንደገና ማደራጀት እንዳስፈለገ ተናግረዋል።

ምርታማነትን እና ቅልጥፍናን በማሳደግ ጥራት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት እና በክልሉ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት።

ፈርጀ ብዙ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በመላ የክልሉ ሕዝብ ዘንድ ዘላቂ ቅቡልነት ኖሯቸው እንዲከናወኑ ለማድረግ በሚችሉ ተቋማዊ የማሻሻያ ርምጃዎች ማጀብ እና መደገፍ ተገቢ መኾኑን ገልጸዋል።

የተሻሻለው አዋጅ የነበሩትን ክፍተቶች እንደሚቀርፍ ተናግረዋል። የአንደኛው ተቋም ሥልጣን እና ተግባር ከሌላኛው ጋር የማይጋጭ ግልጽ ዓላማ ይዘው እንዲደራጁም ያስችላል ነው ያሉት።

ተግባር እና ኀላፊነታቸውን ለመውጣት በቅንጅት መሥራት እና ውጤታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ ያደርጋል ተብሏል። ኀላፊነታቸውን ሲያጓድሉ ደግሞ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲቻል የአሥፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት እንደገና ማሻሻል አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል ብለዋል።

የመፈጸም አቅማቸው ያደገ፣ የተረጋጋ እና ተቋማዊ ትውስታ ያለው ተቋም ለመፍጠር፤ ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ጋር አብረው እየተለወጡ ብሎም ራሳቸውን እያሻሻሉ የሚሄዱ ዘመኑን የዋጁ ተቋማትን ማደራጀት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

አዋጁ ለኅብረተሰቡ ቀልጣፋ እና የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስች ነውም ተብሏል። የአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱን መፈጸም የሚያስችል እንደኾነም ተጠቁሟል።

በተሻሻለው የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ ሥልጣን እና ተግባራት መወሰኛ አዋጅ መሠረት የተቋቋሙ አሥፈጻሚ አካላት:-

1.ግብርና ቢሮ
2. ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ
3. ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ
4. መሬት ቢሮ
5. የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ
6. የውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ
7. የማዕድን ቢሮ
8. የመንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ
9. የሥራ እና ክህሎት ቢሮ
10.የገንዘብ ቢሮ
11.የገቢዎች ቢሮ
12. የትምህርት ቢሮ
13.የጤና ቢሮ
14. የፍትሕ ቢሮ
15. የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ
16.የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ
17. የፕላን እና ልማት ቢሮ
18. የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ
19.የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
20. የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ
21. የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ቢሮ
22. የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ
23.,የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን

የስያሜ ለውጥ የተደረገባቸው ተቋማትም፦

👉 የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በዚህ አዋጅ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሚል የስያሜ ለውጥ ተደርጓል።

👉 የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አሥተዳደር የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተብሎ የስያሜ ለውጥ ተደርጓል፤

👉 የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ተብሎ የነበረው በዚህ አዋጅ የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ባለሥልጣን በሚል የስያሜ ለውጥ ተደርጓል፤

👉 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ተብሎ የነበረው በዚህ አዋጅ የኅብረት ሥራ ኮሚሽን በሚል የስያሜ ለውጥ ተደርጓል፤

👉 የዕፅዋት ዘር እና የሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር እና ኳራንታይን ባለሥልጣን ተብሎ ይጠራ የነበረው በዚህ አዋጅ የግብር ጥራት እና ደኅንነት ቁጥጥር ባለሥልጣን በሚል የስያሜ ለውጥ ተደርጓል፡፡

👉 የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ተብሎ የነበረው በዚህ አዋጅ ፕላን ኢንስቲትዩት በሚል የስያሜ ለውጥ ተደርጓል።

👉 የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ተብሎ የነበረው የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት በሚል የስያሜ ለውጥ ተደርጓል፤

በተሻሻለው አዋጅ መሠረት የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተቋቁሟል። የአማራ ክልል ስቴት ዩኒቨርሲቲ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የክልሉ መንግሥት አሥፈፃሚ አካል ኾኖ ነው የተቋቋመው።

በተሻሻለው አዋጅ መሠረት የኮንስትራክሽን ባለሥልጣንም ተቋቁሟል። የክልሉ የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮድ፣ ስታንዳርድ እና ደረጃን መሠረት በማድረግ የክልሉን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮድ፣ ስታንዳርድ እና ደረጃ ያዘጋጃል፤ ያስፈጽማል። ባለ ሥልጣኑ ሌሎች ሰፋ ያሉ ሥልጣን እና ኀላፊነቶች እንደተሰጡትም ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አባላትም አዋጁ ተገቢ፣ ጊዜውን የጠበቀ፣ ባለቤት ለሌላቸው ተቋማት ባለቤት የሰጠ፣ ሥልጣን እና ኀላፊነታቸውን የለየ ነው ብለዋል። ዕቅዱን ለማስፈጸም ቁርጠኛ ሥራ እንደተጀመረም የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል።

በተቋማት እና በመሪዎች መካከል መረጋጋት እንዲኖር፣ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችል ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞላ እና የሚያርም ነው ተብሏል። ከአሁን ቀደም የነበሩት ተቋማት የተግባር እና የኀላፊነት ግጭት የነበረባቸው እንደነበሩ ተነስቷል። አዋጁ የረጅም ጊዜ ልማትን እና ዕቅድን ታሳቢ ያደረገ እንደኾነም ገልጸዋል።

የቀደመው አዋጅ የተቋማትን ሥልጣን እና ተግባር የቀላቀለ ስለነበረ ለክትትል እና ለቁጥጥር አስቸጋሪ እንደነበር አንስተዋል።

በተሻሻለው አዋጅ ላይ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን በትኩረት ማየት እንደሚጠበቅም አንስተዋል። በተለይም የተጠሪ ተቋማትን እና እንደገና የተደራጁ ተቋማትን በተገቢው መንገድ መለየት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት የአሥፈጻሚ አካላት አደረጃጀት አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል። ዕቅዱ ተቋማዊ አቅምን እና ክልላዊ ጸጋን መሠረት አድርጎ የታቀደ መኾኑን ተናግረዋል።

የአሥፈጻሚ አካላትን የየራሳቸውን ተልዕኮ ለመወጣት በሚችሉበት መንገድ ማደራጀት፣ እሴት እንዲጨምሩ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ተቋማት ሲደራጁ ለክልሉ እሴት የሚጨምሩ መኾን እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። ጠሪ እና የተጠሪ ተቋማት ግንኙነትም እንደተፈተሸ ገልጸዋል።

ተቋማት ሲደራጁ ወጭ ቆጣቢ መኾን እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት። ተቋማት በሕግ እና በሥርዓት እንዲመሩ፣ ለተቋቋሙለት ዓላማ በመሥራት ውጤማ እንዲኾኑ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ መፈተሽ መቻሉን እና ያን ማስተካከል የሚያስችል ማሻሻያ መደረጉን ነው የተናገሩት። የልማት ድርጅቶች የትርፍ እና ልማትን የሚያፋጥኑ እንዲኾኑ እንደሚፈለግ ገልጸዋል። መሪዎች እና ተቋማት ግልጽ ተልዕኮ እና ኀላፊነት ተሰጥቷቸው እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የታቀደውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ በተገቢው የተደራጀ ተቋም እና ቁርጠኛ መሪ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የተቋማት እና የመሪዎች ምዘና እንደሚኖርም ተናግረዋል። በምዘናው መሠረት ተጠያቂነት እንደሚኖር ገልጸዋል። ምክር ቤቱም ሥራ አሥፈጻሚው የሠራውን ሥራ እየተከታተለ መጠየቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ተልዕኮን መሸከም የሚችል ተቋም ለማደራጀት ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል። በጊዜ የለኝም መንፈስ ወደ ሥራ መግባት ይጠበቃልም ብለዋል።

ምክር ቤቱ በአዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦
Next article“ግባችን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተመጣጠነ እና በቂ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)