የግብዓት እጥረት እንዳጋጠማቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

386

የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ምንም ምርጥ ዘር እንዳልደረሰው አስታውቋል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ በቀጣይ ዓመት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሠራ ገልጿል፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን ሀገር ማሪያም ከስም ወረዳ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች በቂ ግብአት እንዳልቀረበላቸው ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ በተለይም የኤን ፒ ኤስ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን 328 ሺህ አርሶ አደሮች በመኸር እርሻ ይሳተፋሉ፤ 49ሺህ 900 ሄክታር መሬት ደግሞ ይታረሳል፤ 1 ሚሊዮን 16 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በማሰራጨት ደግሞ 18 ነጥብ 5 ሚ ኩንታል ምርት ለማምረት ዕቅድ ተይዟል፡፡

በዞን ከሚመረቱ ዋና ዋና የሰብል ምርቶች መካከል ጤፍ፣ ስንዴ እና ገብስ ተጠቃሽ መሆናቸውን ከዞኑ ግብርና መመሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከአነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ማሙየ ንጉሤ እና አቶ ዝጋርጌ አጥላዉ ደግሞ የሀገረማሪያም ከሰም ወረዳ የጥደሽ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በመኸር እርሻ እያንዳንዳቸዉ ከሁለት ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት አላቸው፤ እርሻቸውንም ደጋግመው በማረስ ዝግጁ አድርገዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ከአንድ ሄክታር መሬት የሦስት ኩንታል ምርት ጭማሪ ለማገኘት እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን እስካሁን አንድ አንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ብቻ አግኝተዋል፡፡

የሀገረማሪያም ከሰም ወረዳ ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በቀለ ሺፈራው በባለፈው ዓመት በወረዳው 84 ሺህ 480 ኩንታል ምርት ማገኘቱን አስታውሰው በተያዘው የምርት ዘመን ደግሞ 16 በመቶ የምርት ጭማሪ ለማምጣት ከአርሶ አደር እስከ ባለሙያ በመግባባት ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ 22 ሺህ 570 ሄክታር መሬት እየታረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምርት ዘመኑ 45 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዶ እስከ አሁን 31 ሺህ 400 ኩንታል ገብቷል፤ ከገባው ደግሞ ለ20 ቀበሌዎች 23 ሺህ 429 ኩንታል መሰራጨቱን አብራርተዋል፡፡ በስርጭት ወቅት የኤን ፒ ኤስ ማዳባሪያ እጥረት በመከሰቱ የዞን ግብርና መመሪያን ተጨማሪ ግብዓት እንዲያቀርብ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ በምርት ዘመኑ ስንዴ 500 ኩንታል፣ የቢራ ገብስ 300 ኩንታል ለማስገባት በዕቅድ ቢያዝም እስከ አሁን ለወረዳ የቀረበለት ምንም ምርጥ ዘር አለመኖሩን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡ እጥረቱ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ አርሶ አደሩ በማበጠር እና የተሻሉ ዘሮችን በልውውጥ ገዝቶ እንዲዘራ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መመሪያ ኃላፊ መሠረት ኃይሌ በበኩላቸው በዞኑ 84 ሺህ 885 የከረመ እና 931 ሺህ 501 የአፈር ማዳበሪያ በአዲስ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡ በአዲስ ለማቅርብ በዕቅድ ከተያዘው 747 ሺህ 677 ኩንታል (80 በመቶ ቀርቧል)፤ ከተሰራጨው የአፈር ማዳበሪያ 355 ሺህ 894 ኩንታል እጅ በእጅ ክፍያ፣ 123 ሺህ 112 ኩንታል ደግሞ በብድር መሰጡቱን ወይዘሮ መሠረት ተናግረዋል፡ 183 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ ገና ከወደብ ተጓጉዞ እንዳልቀረበላቸው ነው ያስታወቁት፡፡

እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ በዞኑ የሚገኙት ወደራ፣ መንዝ፣ ይፋት እና ከሰም የኅብርት ሥራ ዩኒየኖች የቀረበውን የአፈር ማዳበሪ አጓጉዘው አጠናቅቀዋል፡፡ ቀሪው ወደ ዞኑ እስከሚገባ ድረስ ደግሞ ዘግይተው የሚዘሩ አርሶ አደሮች ቀድመው ለሚዘሩ አርሶ አደሮች እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ከምርጥ ዘር አንፃር ደግሞ በምርት ዘመኑ 15 ሺህ 291 ምርጥ ዘር ለማቅርብ በዕቅድ ተይዟል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ስንዴ 6 ሺህ 157፤ ገብስ 270 ኩንታል መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሩ በሚፈልገው ልክ ምርጥ ዘር ማግኘት እንዳልቻለም አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት በዞኑ የዘር ብዜት አማራጮችን ወደ ሥራ ለማስገባት የመሬት ልየታ እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ መሠረት አስታውቀዋል፡፡ የዘንድሮውን የምርጥ ዘር እጥረት ለመቅረፍ የተቀመጠ የመፍትሔ ሐሳብ ግን አርሶ አደሩ በእጁ ያሉ ዘሮችን መርጦ እንዲጠቀም ነው፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበድሬዳዋ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ ላይ መረባረብ እንደሚገባ የአስተዳደሩ ከንቲባ አሳሰቡ፡
Next articleበስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ 50 ሺህ ሀገር በቀል ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡